እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ወደምሰጣችሁ ወደ ከነዓን ምድር በምትገቡበት ጊዜ በዚያ አገር በሚገኝ በአንድ ቤት ውስጥ ሻጋታ ሳሠራጭ፥ የሻጋታው ምልክት በራሱ ቤት ውስጥ መኖሩን የተገነዘበ ማንም ሰው ሄዶ ለካህኑ ‘በቤቴ ሻጋታ መሰል ነገር አለ’ ብሎ ይንገር፤ ካህኑም ሄዶ የሻጋታውን ዐይነት ከመመርመሩ በፊት በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዲወጣ ትእዛዝ ይስጥ፤ አለበለዚያ በቤቱ ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ካህኑ ወደ ቤት ገብቶ ይመርምር፤ የሻጋታውን ዐይነት በሚመረምርበት ጊዜ ግድግዳውን እየቦረቦሩ የሚበሉት አረንጓዴ ወይም ቀይ ዐይነት ዝንጒርጒር ምልክቶች ቢታዩበት፥ ከዚያ ቤት ወጥቶ ለሰባት ቀን እንዲዘጋ ያድርገው። በሰባተኛው ቀን ተመልሶ መጥቶ እንደገና ይመርምረው፤ የሻጋታው ምልክት ተስፋፍቶ ቢገኝ፥ የሻጋታው ምልክት ያለባቸው ድንጋዮች ተፈልፍለው ወጥተው ከከተማው ውጪ በሚገኘው በረከሰ ጒድፍ ማከማቻ እንዲጣሉ ይዘዝ። ከዚያም በኋላ የውስጡ ግድግዳ ሁሉ እንዲፋቅና ምርጊቱ ሁሉ ተቀርፎ ከከተማ ውጪ በሚገኘው በረከሰ ጒድፍ መጣያ እንዲጣል ያድርግ። ከዚህም በኋላ በእነዚያ በቀድሞዎቹ ድንጋዮች ምትክ ሌሎች አዳዲስ ድንጋዮች ተገንብተው ቤቱ በአዲስ ጭቃ ይመረግ። “ድንጋዮቹ ተወግደው፥ ግድግዳው ተፍቆ፥ ምርጊቱም ተነሥቶ ቤቱ በዐዲስ ጭቃ ተመርጎ ከታደሰ በኋላ የሻጋታው ምልክት እንደገና ቢታይ፥ ካህኑ ሄዶ ይመልከተው፤ የሻጋታው ዐይነት የሚስፋፋና የማይለቅ ሻጋታ ስለ ሆነ ቤቱ ርኩስ ነው። ስለዚህ መፍረስ አለበት፤ ድንጋዮቹ እንጨቱና ምርጊቱ ሁሉ ከከተማ ውጪ ተወስዶ በረከሰ ጒድፍ ማከማቻ ስፍራ ይጣል፤ ከተዘጋ በኋላ ወደዚያ ቤት የገባ ሰው ሁሉ እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ በዚያ ቤት ውስጥ የተኛ ወይም ምግብ የተመገበ ቢኖር ልብሱን ይጠብ። “ቤቱ እንደገና ታድሶ ከተለሰነ በኋላ ካህኑ መጥቶ በሚመለከትበት ጊዜ ሻጋታው የመስፋፋት ምልክት የማያሳይ ሆኖ ከተገኘ ግን የሻጋታው ምልክት ጨርሶ ስለ ጠፋ ያ ቤት ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ ጥቂት የሊባኖስ ዛፍ እንጨት፥ የቀይ ከፈይ ክርና የሂሶጵ ቅጠል ይውሰድ። ከወፎቹ አንዱን ንጹሕ የምንጭ ውሃ ባለበት የሸክላ ዕቃ ላይ ይረደው፤ ከዚያም በኋላ የሊባኖሱን ዛፍ እንጨት፥ የሂሶጱን ቅጠል፥ የቀዩን ከፈይ ክርና በሕይወት ያለውን ወፍ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውሃ ውስጥ ይንከረው፤ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይርጨው። በዚህም ዐይነት ካህኑ ያንን ቤት በወፉ ደም፥ በንጹሑ ውሃ፥ ሕይወት ባለው ወፍ፥ በሊባኖሱ ዛፍ እንጨት በሂሶጱ ቅጠልና በቀዩ የከፈይ ክር እንዲነጻ ያደርገዋል። ከዚያም በኋላ በሕይወት ያለውን ወፍ ከከተማ ውጪ ወደ ሜዳ እንዲበር ይለቀዋል፤ በዚህም ዐይነት ለቤቱ የማንጻት ሥርዓት ይፈጽማል፤ ቤቱም ንጹሕ ይሆናል። “እነዚህም ለማንኛውም ተላላፊ ለሆነ የሥጋ ደዌ በሽታ፥ ለእከክ የሥርዓት መመሪያዎች ናቸው። በልብስና በቤት ላይ የሚወጣ ሻጋታን፥ እባጭን፥ ሽፍታንና ቋቊቻን ለማንጻት የወጡ ሕጎች ናቸው። እነዚህ ሥርዓቶች አንድን ነገር ንጹሕ መሆኑን ወይም አለመሆኑን የሚወስኑ ናቸው።”
ኦሪት ዘሌዋውያን 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 14:33-57
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች