የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 7

7
1“ሰዎች ሁሉ በምድር ላይ እንደ ግዳጅ ሠራተኞች አይደሉምን?
ቀኖቻቸው እንደ ቅጥር ሠራተኞች ቀኖች አይደሉምን?
2እነርሱም በጥላ ሥር ለማረፍ እንደሚፈልጉ አገልጋዮችና
ደመወዛቸውን ለመቀበል እንደሚጠባበቁ ሙያተኞች አይደሉምን?
3የድካም ወሮቹ ለእኔ ጥቅም የለሽ ሆኑ፤
የችግር ሌሊቶቹም ለእኔ የጭንቅ ሌሊት ሆኑብኝ።
4በምተኛበት ጊዜ መቼ
እነሣ ይሆን ብዬ አስባለሁ፤
ሌሊቱ ግን ይረዝምብኛል፤
እኔም እስኪነጋ ድረስ ስገላበጥ ዐድራለሁ።
5መላ ሰውነቴ በትል ተሞልቶአል፤
ሥጋዬም በቅርፊት ተሸፍኖአል፤
ፈንድቶም ይመግላል።
6የዕድሜዬ ቀኖች ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ ይፈጥናሉ፤
ያለ አንዳች ተስፋም ወደ ፍጻሜ ይደርሳሉ።
7አምላክ ሆይ! ሕይወቴ ከትንፋሽ ያጠረ መሆኑን አስታውስ፤
ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ መልካም ነገርን አላይም።
8“አሁን የሚያየኝ ዳግመኛ አያየኝም፤
ቢፈልገኝም እንኳ ሊያገኘኝ አይችልም።
9ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ ሁሉ፥
ሞቶ ወደ ሙታን ዓለም የሚሄድ ሰው ተመልሶ አይመጣም፤
10እንደገናም ወደ ቤቱ አይመለስም፤
የሚያውቁት ሁሉ ይረሱታል።
11ከእንግዲህ ወዲህ ዝም አልልም!
ከመንፈስ ጭንቀቴ የተነሣ እናገራለሁ፤
ከነፍሴ ምሬት የተነሣ አጒረመርማለሁ።
12“ይህን ያኽል ተጠባባቂ ያደረግህብኝ
እኔ ባሕር ነኝን? ወይስ ዓሣ አንበሪ?
13‘አልጋዬ ያጽናናኛል፤
መኝታዬ ሕመሜን ያስታግሥልኛል፤’
ብዬ አሰብኩ፤
14አንተ ግን በሕልም ታስፈራኛለህ፤
በቅዠትም ታስደነግጠኛለህ።
15ይህን ሥቃይ የበዛበት ሰውነት ተሸክሜ ከመኖር
ታንቄ መሞትን እመርጣለሁ።
16ተስፋ ቈርጬአለሁ፤ መኖርም አልፈልግም፤
የሕይወቴም ዘመን አጭር ስለ ሆነ ተወኝ።
17“ግምት ትሰጠው ዘንድና
ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? #መዝ. 8፥4፤ 14፥3።
18በየማለዳውስ ትመረምረው ዘንድ
በየጊዜውስ ትፈትነው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?
19ምራቄን እስክውጥ እንኳ
ለጥቂት ጊዜም አትተወኝምን?
20አንተ ሰዎችን በመቈጣጠር የምትከታተል አምላክ ሆይ፥
እኔ ኃጢአት በመሥራቴ አንተ ምን ተበደልክ?
ስለምን ዒላማ አደረግኸኝ?
ይህን ያኽል ከባድ ሸክም ሆንኩብህን?
21ከቶ ኃጢአቴን ይቅር አትልልኝምን?
የማደርገውንስ በደል አትደመስስልኝምን?
ወደ መቃብር መውረጃዬ ደርሶአል፤
ከእንግዲህ ወዲህ ብትፈልገኝ እንኳ አልገኝም።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ