መጽሐፈ ኢዮብ 8
8
ቤልዳድ
1የሹሐ አገር ሰው የሆነው ቢልዳድ እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፦
2ከአንደበትህ የሚወጡት ቃላት እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው፤
እስከ መቼ ድረስ እንደዚህ አድርገህ ትናገራለህ?
3እግዚአብሔር ፍርድን ከቶ አያጣምምም፤
ሁሉን ቻይ አምላክ ሁልጊዜ ትክክለኛውን ነገር ያደርጋል።
4ልጆችህ እግዚአብሔርን በድለውት ከሆነ፥
እነርሱ ቅጣታቸውን አግኝተዋል ማለት ነው።
5ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ብትመለስ፥
ሁሉን ቻዩን አምላክ ብትለምነው፥
6ቀጥተኛና ንጹሕ ከሆንክ፥
እርሱ ፈጥኖ
ወደ ተገቢ ቦታህ ይመልስሃል።
7አጀማመርህ አነስተኛ መስሎ ቢታይም፥
የወደፊት ኑሮህ የተትረፈረፈ ይሆናል።
8“እስቲ የጥንቱን ትውልድ ጠይቅ
የቀድሞ አባቶቻቸውን ልምድ ተመራመር።
9የእኛ ዕድሜ ገና ትንሽ በመሆኑ
ምንም አናውቅም፤ ዕድሜአችንም እንደ ጥላ የሚያልፍ ነው።
10እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ ካስተዋሉት አፍልቀው አይደለምን?
11በውኑ ረግረግ ባልሆነ ቦታ ደንገል ይበቅላልን?
ውሃስ በሌለበት ቦታ ሸምበቆ ይለመልማልን?
12ይህ ካልሆነ አድገው ለመቈረጥ ከመብቃታቸው በፊት
ከማንኛውም አረንጓዴ ተክል ቀድመው ይደርቃሉ።
13እግዚአብሔርን የሚረሱ ሰዎች ሁሉ ፍጻሜአቸው ልክ እንደዚሁ ነው፤
እግዚአብሔር የለም የሚሉ ሰዎች ተስፋቸው ይቈረጣል።
14እንደ ሸረሪት ድር በሚበጠስ ነገር ይታመናሉ፤
ተስፋ የሚያደርጉበት ነገር እንኳ ቢኖር በቀላሉ ይጠፋል።
15በሸረሪቱ ድር ላይ ቢደገፍ ጸንቶ አይቆምም፤
የሸረሪት ድሩን ቢጨብጥ ይበጠስበታል።
16“አረም በፀሐይ አቈጥቊጦ በአትክልት ቦታው እንደሚበዛ
ክፉ ሰዎችም እንደዚሁ ይበዛሉ።
17ሥሮቹም በድንጋይ ካብ ላይ ይጠመጠማሉ፤
በየቋጥኙም ላይ ይጣበቃሉ።
18አንድ ሰው ከቦታው ቢነቅለው
የነበረበት ቦታ አይታወቅም።
19አረሙም በዚህ ዐይነት ይደርቃል፤
ሌሎች አትክልቶችም ከመሬት ያቈጠቊጣሉ።
20“እግዚአብሔር ደጋግ ሰዎችን አይጥላቸውም፤
ክፉዎችንም አይረዳቸውም።
21ስለዚህ አንተንም በደስታ እንድትስቅና
‘እልል’ እንድትል ያደርግሃል።
22የሚጠሉህ ሰዎች ግን የኀፍረት ሸማ ይከናነባሉ፤
የክፉ ሰዎችም ቤቶች ይጠፋሉ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 8: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997