መጽሐፈ ኢዮብ 40
40
1ቀጥሎም እግዚአብሔር ኢዮብን እንዲህ አለው፦
2“ኢዮብ ሆይ! ለመሆኑ ሰው ሁሉን ከሚችል አምላክ ከእኔ
ጋር ተከራክሮ ሊረታ የሚችል ይመስልሃልን?
ከእኔ ከእግዚአብሔር ጋር የምትከራከር አንተ ስለ ሆንክ፥
እስቲ መልስ ስጥ።”
ኢዮብ
3ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፦
4“ጌታ ሆይ! እኔ ለምንም የማልጠቅም ከንቱ ሰው ነኝ፤
ከእንግዲህ ወዲህ አፌን በእጄ ይዤ ዝም ከማለት በስተቀር፥
ለአንተ የምሰጠው መልስ የለኝም።
5አንድ ጊዜ፥ ወይም ሁለት ጊዜ ተናገርኩ፤
ከእንግዲህ ወዲያ ከቶ አልናገርም።
እግዚአብሔር
6ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ኢዮብን እንዲህ አለው፦
7“ተነሥና እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤
እጠይቅሃለሁ፤ አንተም መልስልኝ።
8እኔን ፍርደ ገምድል አድርገህ በመክሰስ
ራስህን ንጹሕ ለማድረግ ትሞክራለህን?
9ለመሆኑ ኀይልህ እንደ እኔ እንደ እግዚአብሔር ኀይል የበረታ ነውን?
ድምፅህስ እንደ እኔ እንደ እግዚአብሔር ድምፅ ኀያል ነውን?
10ይህ ከሆነ ራስህን በግርማ ሞገስ ተቀዳጅ
ክብርንና ገናናነትንም ተጐናጸፍ።
11ትዕቢተኞችን ተመልክተህ አዋርዳቸው፤
ቊጣህንም በላያቸው አፍስስ።
12በጥንቃቄ ሁሉን ተመልክተህ አሳፍራቸው፤
ክፉዎችንም ባሉበት ስፍራ አጥፋቸው።
13በከፈን ጨርቅም ጠቅልለህ
ሁሉንም በአንድነት በመሬት ውስጥ ቅበራቸው።
14ከዚያ በኋላ እኔም በተራዬ
በራስህ ኀይል ድልን እንደምትቀዳጅ እመሰክርልሃለሁ።
15“እኔ አንተንና ጒማሬን ፈጥሬአለሁ፤
ጉማሬውም እንደ በሬ ሣር ይበላል።
16በወገቡ ላይ ያለውን ጥንካሬና
በሆዱ ውስጥ ያለውን የጅማት ብርታት ተመልከት።
17ጅራቱ እንደ ሊባኖስ ዛፍ ቀጥ ያለ ነው፤
የጭኑም ጅማት ወፍራምና ጠንካራ ነው።
18አጥንቶቹ እንደ ነሐስ ናቸው።
እንደ ብረት ዘንጎችም የጠነከሩ ናቸው።
19“እኔ ከፈጠርኳቸው ፍጥረቶች ሁሉ ኀያል
ከእኔ በቀር የሚያሸንፈው የለም።
20የዱር እንስሶች የሚፈነጩበት ተራራ
ለእርሱ ምግብን ያበቅልለታል።
21ጥላ ካለው ዛፍና በደንገል መካከል
በረግረግ ውስጥ ይተኛል።
22ጥላ ያላቸው ዛፎች በጥላው ይሰውሩታል።
የአኻያ ዛፎችም ይከቡታል።
23በወንዝ ውሃ ሙላት ከቶ አይደነግጥም፤
የዮርዳኖስ ወንዝ እንኳ እስከ አፉ ቢጐርፍበት አይሰጋም፥
24ዐይኑን በማጥፋትና አፍንጫውን በመሰነግ፥
ጒማሬን ሊይዘው የሚችል ማነው?
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 40: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997