የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 39

39
1“የበረሓ ፍየሎች የሚወልዱበትን ጊዜ ታውቃለህን?
ዋልያ አምጣ ስትወልድ አይተህ ታውቃለህን?
2በእርግዝና ምን ያኽል ጊዜ እንደምትቈይ፥
መቼስ እንደምትወልድ ታውቃለህን?
3ተንበርክካ በማማጥ ግልገሎችዋን የምትወልደው
መቼ እንደ ሆነ ታውቃለህን?
4ግልገሎችዋ በዱር አድገው ይጠነክራሉ፤
ወጥተውም ከሄዱ በኋላ፥ ዳግመኛ ወደ እናታቸው አይመለሱም።
5“ለሜዳ አህዮች ነጻነት የሰጣቸው ማን ነው?
ከእስራት የፈታቸውስ ማን ነው?
6በረሓን ለእነርሱ መሰማሪያ አድርጌ ሰጥቼአለሁ፤
ጨው ባለበት ሜዳም እንዲኖሩ አድርጌአቸዋለሁ።
7ሁካታ ከበዛባቸው ከተሞች ርቀው ይኖራሉ፤
ከኋላ እየነዳ የሚጮኽባቸውን አይቀበሉም።
8በተራሮች ላይ ይሰማራሉ፤
በዚያም ምግብ የሚሆናቸው ለምለም ሣር ይፈልጋሉ።
9“ጎሽ የተባለው የዱር እንስሳ
አንተን ለማገልገል ፈቃደኛ ይሆናልን?
በበረትህስ ውስጥ ሊያድር ይችላልን?
10ጐሽን ጠምደህ ሞፈር እየጐተተ
እንዲያርስ ልታደርገው ትችላለህን?
11ስለ ብርቱ ጥንካሬው በእርሱ ትተማመናለህን?
ከባድ ሥራህንስ ለእሱ ትተውለታለህን?
12ወደ አንተ እንደሚመለስና
ሰብልህን ወደ አውድማ እንደሚያመጣልህ ትተማመንበታለህን?
13“ሰጎን ክንፎችዋን በፍጥነት ትዘረጋለች፤
ነገር ግን እንደ ሸመላ አትበርም።
14ሰጎን እንቊላልዋን በምድር ላይ ትጥላለች፤
በዐፈር ላይ ተቀምጦም እንዲሞቅ ታደርጋለች።
15‘በዚያ የሚያልፍ በእግሩ ይሰብረዋል፤
የዱር አውሬም ረግጦ ያደቀዋል’ ብላ አታስብም።
16ጫጩቶችዋ የእርስዋ እንዳልሆኑ አድርጋ ትጨክንባቸዋለች፤
ድካምዋ ሁሉ በከንቱ ቢቀር ደንታ የላትም።
17እንደዚህ ጥበብ የነሣኋትና
ሞኝ እንድትሆን ያደረግኋት እኔ ነኝ።
18ተነሥታ በምትሮጥበት ጊዜ ግን፥
ፈረስና ፈረሰኛው ሊወዳደሩአት ቢሞክሩ ትስቅባቸዋለች።
19“ኢዮብ ሆይ! ለፈረሶች ኀይልን የሰጠህ፥
በረጃጅምም ጋማ ያስጌጥካቸው አንተ ነህን?
20እንደ አንበጣ እየዘለሉ በማንኮራፋት
ሰውን እንዲያስደነግጡ የምታደርጋቸው አንተ ነህን?
21ፈረሶቹ ወደ ጦር ሜዳ ተጋልበው ሲሄዱ
በጒልበታቸው በመመካት ሶምሶማ ይረግጣሉ።
22ፍርሀት የሚባል ነገር ከቶ አያውቁም፤
ምንም ነገር አያስደነግጣቸውም፤
ሰይፍ ቢመዘዝባቸው እንኳ ወደ ኋላ አይመለሱም።
23የሚጋልቡአቸው ጦረኞች የያዙአቸው የጦር መሣሪያዎች
በፀሐይ እየተብለጨለጩ እርስ በርሳቸው ሲፋጩ ይሰማል።
24እምቢልታው ሲነፋ ሲቃ ይዞአቸው
በጭካኔና በቊጣ ወደ ጦር ሜዳ ይሸመጥጣሉ።
25እምቢልታ በተነፋ ቊጥር በደስታ ያናፋሉ፤
በሩቅ ሆነው ጦርነቱን በሽታ ያውቃሉ፤
የጦር አዛዦች የሚሰጡትን ትእዛዝና
የሠራዊቱን ድንፋታ ይሰማሉ።
26በውኑ ጭልፊት የሚያንዣብበው፥
ክንፎቹንም ወደ ደቡብ የሚዘረጋው በአንተ ጥበብ ነውን?
27ንስርን ወደ ላይ ወጥቶ
በከፍተኛም ቦታ ላይ ጎጆውን የሚሠራው አንተ አዘኸው ነውን?
28ንስር በቋጥኞች መካከል ይኖራል፤ እዚያም ጎጆውን ይሠራል።
ቋጥኞቹም መከላከያ ይሆኑለታል።
29እዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ነገር ያማትራል፤
ዐይኖቹም በሩቅ ያለውን ያያሉ።
30በዚህ ዐይነት ንስሮች በበድን ዙሪያ ይሰበሰባሉ፤
ጫጩቶቻቸውም ደሙን ይጠጣሉ።” #ማቴ. 24፥28፤ ሉቃ. 17፥37።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ