መጽሐፈ ኢዮብ 38
38
የእግዚአብሔር መልስ
1ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ኢዮብን እንዲህ አለው፦
እግዚአብሔር
2“ይህ፥ ያለ ዕውቀት በሚነገሩ ቃላት
ምክሬን የሚያቃልል እርሱ ማነው?
3እስቲ በፊቴ እንደ ወንድ ታጠቅ፤
እጠይቅሃለሁ፤ አንተም መልስልኝ።
4ለመሆኑ ዓለምን ስፈጥር
አንተ በዚያ ነበርክን?
የምታውቅና የምታስተውል ከሆነ እስቲ ንገረኝ።
5የምድርን መጠን የወሰነ ማን ነው?
በእርሱዋ ላይስ የመለኪያ መስመሮችን
የዘረጋ ማን እንደ ሆነ ታውቃለህን?
6የምድርን ምሰሶዎች አጽንቶ የያዘ ኀይል ምንድን ነው?
የዓለምንስ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠ ማን ነው?
7የንጋት ከዋክብት በአንድነት ሲዘምሩ፥
መላእክትም ሁሉ እልል ሲሉ አንተ የት ነበርክ?
8“ከምድር ውስጥ ፈንድቶ በወጣ ጊዜ
የመፍለቂያ በሮቹን የዘጋ ማነው?
9ባሕርን በደመና የጋረድኩ
በድቅድቅ ጨለማም የሸፈንኩ እኔ ነኝ።
10ለባሕር ወሰንን የሠራሁ፥
በርና ገደብም እንዲኖረው ያደረግኹ እኔ ነኝ።
11እስከዚህ ድረስ ትመጣለህ!
ከዚህም አታልፍም! የአንተም ብርቱ ማዕበል
እዚህ ይቁም! ያልኩ እኔ ነኝ። #ኤር. 5፥22።
12ኢዮብ ሆይ!
በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ከቶ ንጋትን አዘህ ታውቃለህን?
ለንጋት ወገግታስ ቦታ መድበህለታልን?
13ንጋት በምድር ላይ ብርሃን እንዲያሳይ፥
ክፉ ሰዎችንም ከተደበቁበት ቦታ እንዲያጋልጥ
ትእዛዝ ሰጥተህ ታውቃለህን?
14የንጋት ብርሃን ኰረብቶችንና ሸለቆዎችን እንደ ተጣጠፈ ልብስ ቈመው እንዲታዩ ያደርጋቸዋል፤
በሸክላ ላይ እንዳለ መኅተምም አጒልቶ ያሳየዋል።
15ክፉዎች ብርሃን ተከልክለዋል፤
ለዐመፅ ያነሡአቸው ክንዶቻቸውም ተሰብረዋል።
16“ወደ ባሕሩ ጥልቀት ወርደሃልን?
በውቅያኖስ ወለል ላይ ተመላልሰህ ታውቃለህን?
17የሞትን በሮች እንድታይ ተደርገሃልን?
የድቅድቅ ጨለማንስ መዝጊያ አይተሃልን?
18ዓለም ምን ያኽል ትልቅ እንደ ሆነች ማወቅ ትችላለህን?
እስቲ ይህን ሁሉ ታውቅ እንደ ሆነ ንገረኝ።
19“ወደ ብርሃን የሚወስደውን መንገድ
ጨለማስ የት እንደሚኖር ታውቃለህን?
20ብርሃንንና ጨለማን ወደየቦታቸው ልትወስዳቸው ትችላለህን?
ወደ መኖሪያቸው የሚወስደውን መንገድ ታውቃለህን?
21ዓለም በተፈጠረ ጊዜ ተወልደህ ስለ ነበረ በእርግጥ ታውቃለህ!
ዕድሜህም በጣም የገፋ ነው!
22“ወደ በረዶ ማስቀመጫ ቤት ገብተሃልን?
ወይስ የተቀመጠውን የበረዶ ክምችት አይተሃልን
23ይህም በረዶ እኔ በጦርነትና በውጊያ ላይ እንድጠቀምበት
ለችግር ጊዜ ያስቀመጥኩት ነው።
24ብርሃን የሚከፋፈልበት ቦታ ወዴት ነው?
ወይስ ደረቅ ነፋስ በምድር ላይ የሚሠራጭበት ቦታ ወዴት ነው?
25“ለዝናብ መውረጃን ያዘጋጀለት፥
ነጐድጓድ ለተቀላቀለበት ውሽንፍርም
መንገድ ያበጀለት ማነው?
26እንዲሁም ማንም በሌለበት ምድር፥
ሰው በማይኖርበት ምድረ በዳ፥
27ዝናብ እንዲዘንብ የሚያደርግ ማነው?
ጠፍና ባድማ የሆነውን መሬት ረስርሶ
ምድሩንም ሣር እንዲያበቅል ያደረገው ማነው?
28ዝናብንና ጤዛን
የሚያስገኝ ማነው?
29በረዶንና አመዳይን
የሚያስገኝ ማነው?
30ውርጩ ውሃን እንደ ድንጋይ ያጠጥራል፤
የባሕሩም ወለል እንደ በረዶ እንዲረጋ ያደርገዋል።
31“ ‘ፕልያዲስ’ የተባሉትን ከዋክብት በአንድነት ማሰር ትችላለህን?
ኦርዮን የተባሉትንስ ከዋክብት የተያያዙበትን ገመድ መበጠስ ትችላለህን? #ኢዮብ 9፥9፤ አሞጽ 5፥8።
32ከዋክብትን ሁሉ በየወቅታቸው ማሰማራት ትችላለህን?
የድብ ቅርጽ ያላቸውን ከዋክብትስ ከልጆቻቸው
ጋር መምራት ትችላለህን?
33ሰማያት በምን ዐይነት ሥርዓት እንደሚተዳደሩ ታውቃለህን?
ይህንንስ ደንብ በምድር ላይ እንዲሠራ ለማድረግ ትችላለህን?
34“ብዙ ዝናብ እንዲያዘንብልህ፥
ደመናን ልታዘው ትችላለህን?
35መብረቅ በአንተ ትእዛዝ ይበርቃልን?
36ለልብ ጥበብን
ለአእምሮስ ማስተዋልን የሰጠ ማነው?
37-38በጥበቡ ደመናን ለመቊጠር የሚችል ማነው?
የተሰበሰበው ዐፈር ርሶ ጭቃ እንዲሆን
ከማከማቻው ከሰማይ ውሃ ወደታች ለማፍሰስ የሚችል ማነው?
39በጫካው ውስጥ ታጋድመውና አድብተው ሳሉ
ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን?
40የተራቡ ልጆችዋንስ መመገብ ትችላለህን?
41ልጆችዋ ምግብ አጥተው ሲቅበዘበዙ
ወደ እኔም ሲጮኹ
ለቁራ ምግብ የሚሰጣት ማነው?”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 38: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997