የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 37

37
1“በውሽንፍሩም ኀይል ልቤ ተንቀጠቀጠ፤
በፍርሃትም ተርበደበደ።
2ከአፉ የሚወጣውን ድምፅ ስሙ
እንደ ነጐድጓድ የሚያጒረመርመውን ቃሉን አድምጡ።
3መብረቁን ከሰማይ በታች ሁሉ ያሠራጫል፤
እስከ ምድር ዳርቻም ድረስ ይልካል።
4ከዚህም በኋላ ኀይለኛ ድምፁን ያስገመግማል፤
የሚያስፈራ ድምፁንም እንደ ነጐድጓድ ያሰማል፥
የመብረቁም ብልጭታ ደጋግሞ ይታያል።
በግርማዊ ድምፁም ነጐድጓድን ያሰማል፤
ድምፁን በሚያሰማበት ጊዜ መብረቁን አያግድም።
5እግዚአብሔር አስደናቂ በሆነ ድምፁ ነጐድጓድን ያሰማል፤
እኛ ልንረዳው የማንችል ታላላቅ ነገሮችንም ያደርጋል።
6በረዶ በምድር ላይ እንዲወርድ ያደርጋል፤
ብርቱ ዝናብም እንዲዘንብ ያዛል።
7እርሱ የፈጠራቸው ሰዎች የእርሱን ሥራ እንዲያውቁ፥
ሰዎች ሁሉ ሥራቸውን እንዲያቆሙ ያደርጋል።
8በዚያን ጊዜ የዱር አውሬዎች
ሸሽተው ወደየመሸሸጊያቸው ይገባሉ፤
በየዋሻቸውም ውስጥ ይሰወራሉ።
9ብርቱ ነፋስ ከደቡብ ይነሣል።
ብርዳማ ነፋስም ከሰሜን ይመጣል።
10የእግዚአብሔር እስትንፋስ ውሃን ያቀዘቅዛል፤
ወደ በረዶም ይለውጠዋል።
11ደመና ውሃ እንዲሸከም ያደርጋል፤
በውስጡም መብረቅን ያበርቃል።
12ደመናዎች በጌታ መሪነት በምድር ዙሪያ ይዞራሉ፤
የሚያግዛቸውንም ትእዛዞች ይፈጽማሉ።
13እግዚአብሔር ዝናብን የሚያዘንበው፥
ምድርን ለማረስረስ፥
ሰዎችን ለመቅጣት፥
ወይም ፍቅሩን ለመግለጥ ነው።
14“ኢዮብ ሆይ! እስቲ ዝግ ብለህ አድምጥ፤
እግዚአብሔር የሚያደርጋቸውንም ድንቅ ሥራዎች
ልብ ብለህ አስተውል።
15እግዚአብሔር ደመናን እንዴት እንደሚቈጣጠር፥
መብረቅንም እንዴት እንደሚያበርቅ ታውቃለህን?
16ደመናን በሕዋው ላይ የሚያንሳፍፈውንና
ሁሉን የሚያውቀውን የአምላክን ድንቅ ሥራ ታውቃለህን?
17ሰማዩ ነሐስ በመሰለ ጊዜ
አንተ በኀይለኛው የበረሓ ነፋስ በሙቀት ትቀልጣለህ።
18እግዚአብሔር ሰማይን እንደ ቀለጠ መስተዋት ቢዘረጋ፥
አንተ በአጠገቡ ሆነህ ትረዳዋለህን?
19አእምሮአችን ጨለማ በመሆኑ
ጉዳያችንን ለማቅረብ ስለማንችል፥
ለእግዚአብሔር ምን እንደምለው ንገረን፤
20እግዚአብሔርን ልናገር ብዬ በመጠየቅ
ለምን ያጠፋኝ ዘንድ አነሣሣዋለሁ?
21“ነፋሱ ደመናውን ከሰማይ ላይ በገፈፈው ጊዜ
ማንም ፀሐይን ትኲር ብሎ መመልከት አይችልም።
22ከሰሜን በኩል ወርቅ የመሰለ ብርሃን ይመጣል፤
እግዚአብሔርም በሚያስደንቅ ግርማ ይገለጣል።
23እግዚአብሔር ሊታይ አይቻልም፤
ሥልጣኑም ታላቅ ነው፤
እርሱም ትክክለኛ ፈራጅ ነው።
24በሐሳባቸው ጠቢባን ነን የሚሉትን ስለሚንቃቸው
ሰዎች ሁሉ ይፈሩታል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ