የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 41

41
1“ሌዋታን የሚባለውን የባሕር አውሬ በመንጠቆ ከባሕር ውስጥ ልትይዘው ትችላለህን?
ወይም ምላሱን በገመድ ታስረዋለህን? #መዝ. 74፥14፤ 104፥26፤ ኢሳ. 27፥1።
2በአፍንጫው መሰነጊያ አስገብተህ
መንጋጋውንም በመንጠቆ ወግተህ ልትይዘው ትችላለህን?
3ምሕረት እንድታደርግለት ይለምንሃልን?
በመልካም አነጋገር ይለምንሃልን?
4ለዘለዓለም በባርነት እንዲያገለግልህ
ከአንተ ጋር ስምምነት ያደርጋልን?
5እንደ ወፍ እርሱን ልታለማምድ ትችላለህን?
ወይስ ሴቶች ልጆችህን እንዲያጫውት አስረህ ታኖረዋለህን?
6ዓሣ ነጋዴዎች እርሱን ለመግዛት ይጫረታሉን?
ቈራርጠውስ ይከፋፈሉታልን?
7ቆዳውን በፈለግህበት ቦታ በጦር መብሳት፥
ጭንቅላቱንም በሾተል ወግተህ መሰንጠቅ ትችላለህን?
8ከቻልክ እስቲ እጅህን በላዩ ላይ አሳርፍበት።
ከእርሱ ጋር የምታደርገውን ትግል በፍጹም አትረሳውም፤
ዳግመኛም ከእርሱ ጋር ለመታገል አትሞክርም።
9“ከሌዋታን ጋር ታግሎ በቊጥጥር ሥር ለማዋል የሚደረግ ሙከራ ከንቱ ነው።
እርሱን የሚያየው ሁሉ በፍርሃት ይብረከረካል።
10በእርሱ ላይ አደጋ መጣል ይህን ያኽል አደገኛ ከሆነ፥
ታዲያ፥ እኔን ለመቃወም የሚደፍር ማነው?
11ከሰማይ በታች ያለው ነገር ሁሉ የእኔ ነው፤
ታዲያ፥ እንድመልስለት ለእኔ ያበደረ ማነው?
12“ስለ ሌዋታን እግሮች፥ ስለ ብርቱ ኀይሉ
ስለሚያምረው አካሉ ሳልገልጥ አላልፍም።
13ድርብርብ የሆነ ቆዳውን ለመግፈፍና
መንጋጋውንስ ለመፈልቀቅ ማን ይችላል?
14እጅግ የሚያስፈሩ ጥርሶች ያሉበት አፉን ከፍቶ
መንጋጋውን ሊያላቅቀው የሚችል ማን ነው?
15የጀርባው ቆዳዎች በመደዳ እንደ ተደረደሩ ጋሻዎች ናቸው፤
እጅግ የተጣበቁም ስለ ሆኑ እንደ ብረት ጠንካሮች ናቸው።
16አንዱ ከሌላው ጋር እጅግ የተጣበቀ በመሆኑ፥
በመካከላቸው ነፋስ እንኳ ማለፍ አይችልም።
17ሁሉም እርስ በርሳቸው የተያያዙ ስለ ሆኑ፥
ከቶ ምንም ነገር ሊለያያቸው አይችልም።
18እርሱ በሚያነጥስበት ጊዜ፥
የብርሃን ብልጭታ ይታያል፤
ዐይኖቹም እንደ ንጋት ፀሐይ ያበራሉ፤
19ከአፉ የእሳት ነበልባል ይወጣል፤
የእሳት ፍንጣሪም ሲበተን ይታያል።
20ድስት በተጣደበት ምድጃ ጭራሮ እንደሚጤስ፥
ከአፍንጫው ጢስ ሲወጣ ይታያል።
21የትንፋሹ ግለት ከሰል ያቀጣጥላል፤
የእሳት ነበልባልም ከአፉ ይወጣል።
22የአንገቱ ደንደስ ኀይልን የተሞላ ነው፤
የፊቱም ግርማ እጅግ አስፈሪ ነው።
23ሥጋው ድርብርብ ሆኖ እርስ በርሱ የተጣበቀ ስለ ሆነ
ሰውነቱ እንደ ብረት የጠነከረ ነው።
24ልቡ እንደ ድንጋይ ጠንካራ ነው፤
ጥንካሬውም እንደ ወፍጮ ድንጋይ ነው።
25ይህ አውሬ በሚነሣበት ጊዜ
ኀያላን እንኳ በፍርሃት ይርበደበዳሉ።
26በምንም ዐይነት ሰይፍና፥ ጦር፥ ፍላጻና መውጊያ
ቢያገኙት አያሸንፉትም።
27እርሱ ብረትን እንደ ሰንበሌጥ ይሰባብራል፤
ነሐስንም እንደ በሰበሰ እንጨት ያደቃል።
28ፍላጻ ቢወረወርበት እንኳ ፈርቶ አይሸሽም፤
የወንጭፍ ድንጋይም በእርሱ ፊት እንደ ገለባ ነው።
29እርሱ ዱላን የሚቈጥረው እንደ ሣር ነው፤
ሰዎችም ጦር ሲወረውሩበት በማፌዝ ይስቃል።
30በጭቃ ውስጥ ሲጥመለመል ሹልና ስለ ታም የሆነው ቆዳው፥
እንደ ማረሻ ምድርን ይሰነጣጥቃል።
31ባሕርን እንደ ፈላ ውሃ ያፍለቀልቀዋል፤
በማሰሮ ውስጥ እንደሚፈላ ዘይትም ያንተከትከዋል።
32እርሱ የሚያልፍበት መንገድ ያበራል፤
የባሕሩንም ውሃ ወደ ዐረፋ ይለውጠዋል።
33እርሱ ፍርሀት የማያውቅ ፍጡር ስለ ሆነ፥
በዓለም ላይ እርሱን የሚመስል ፍጡር ከቶ የለም።
34እጅግ ታላላቅ የሆኑትን ፍጡሮች እንኳ ይንቃል፤
እርሱ በአራዊት ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ