የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 33

33
1“አሁንም ኢዮብ ሆይ! የምነግርህን ስማኝ፤
የምልህንም ሁሉ በጥንቃቄ አድምጠኝ፤
2መልስ ልሰጥህ ተዘጋጅቻለሁ፥
አንደበቴም ለመናገር ተዘጋጅቶአል።
3ቃሎቼ የልቤን ቅንነት ይገልጣሉ፤
ምላሶቼም እውነቱን ይናገራሉ።
4የፈጠረኝ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፤
ሕይወትም የሰጠኝ ሁሉን የሚችል አምላክ እስትንፋስ ነው።
5“የምትችል ከሆነ ለንግግሬ መልስ ስጠኝ፤
ክርክሮችህን አመቻችተህ ቆመህ ተከራከረኝ።
6እነሆ፥ እኔና አንተ በእግዚአብሔር ፊት እኩል ነን፤
እኔም የተፈጠርኩት ከጭቃ ነው።
7እኔን መፍራት አይገባህም፤
እኔ ተጽዕኖ ላሳድርብህ አልችልም።
8“በእርግጥ እኔ የተናገርከውን ሁሉ ሳዳምጥ ቈይቼአለሁ፤
ከአንደበትህም የወጡትን ቃላት ሰምቼአለሁ።
9አንተ ስትናገር ‘በደልና እንከን የሌለብኝ፥
ከኃጢአት ንጹሕ የሆንኩ፥ ነጻ ነኝ፤
10ነገር ግን እግዚአብሔር እኔን ለመቅጣት ምክንያት ይፈልግብኛል
እንደ ጠላትም ይቈጥረኛል፥
11እግሮቼን በግንድና በግንድ መካከል አጣብቆ ይይዛል፤
በምሄድበት መንገድ ሁሉ ይመለከተኛል።’ ብለሃል። #ኢዮብ 13፥27።
12“ኢዮብ ሆይ! ይህ ንግግርህ ስሕተት መሆኑን
ልገልጥልህ እወዳለሁ፤
እግዚአብሔር ከሰው ሁሉ ይበልጣል።
13ታዲያ፥ ‘እግዚአብሔር የሰውን አቤቱታ አይሰማም’
በማለት ለምን በእግዚአብሔር ላይ ታማርራለህ?
14ሰው አያስተውልም እንጂ
እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ይናገራል።
15በሌሊት ሰዎች በአልጋ ላይ ተኝተው
አፍላ እንቅልፍ ይዞአቸው ሳለ፥
እግዚአብሔር በሕልምና በራእይ ይናገራል። #ኢዮብ 4፥13።
16በዚያም ጊዜ ሰዎች ቃሉን እንዲሰሙ ያደርጋል፤
በሚሰጣቸውም ማስጠንቀቂያ ያስደነግጣቸዋል።
17በዚህ ዐይነት ሰዎች ኃጢአት ከመሥራት እንዲቈጠቡ ያደርጋል፤
ትዕቢትንም ከእነርሱ ያስወግዳል።
18ሕይወታቸውንም ከጥፋት ይጠብቃል፤
ከሞት መቅሠፍትም ይታደጋቸዋል።
19ወይም እንደገና ሰው በአጥንቱ ውስጥ በማያቋርጥ በሽታ
በአልጋ ቊራኛነት እንዲገሠጽ ያደርጋል።
20በዚህ ዐይነት ሕመምተኛው እህል መቅመስን ያስጠላዋል፤
ምርጥ የሆነ ምግብ እንኳ አያስደስተውም።
21ከመክሳቱ የተነሣ ሥጋው አልቆ
አጥንቱ ወጥቶ ይታያል።
22ሕይወቱ አልፎ
ነፍሱ ወደ ሙታን ዓለም ለመውረድ ተቃርባለች።
23“ለሰው ትክክለኛውን መንገድ ከሚያመለክቱት፥
በሺህ ከሚቈጠሩ የእግዚአብሔር መላእክት አንዱ
ወደ እርሱ መጥቶ ይረዳው ይሆናል፤
24መልአኩም አዝኖለት ‘ቤዛ ያገኘሁለት ስለ ሆነ፥
ወደ መቃብር እንዳይወርድ፥
ተወው!’ ብሎ ሞትን ያዘዋል።
25ስለዚህ ሥጋው እንደገና እንደ ልጅ ሥጋ ሆኖ ይታደሳል፤
እንደ ወጣትነቱም ጊዜ ይመለሳል።
26በዚያን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፤
ጸሎቱንም እግዚአብሔር ይሰማዋል
የእግዚአብሔርን ፊት አይቶ ይደሰታል፤
እግዚአብሔርም ስለጽድቁ ዋጋውን ይከፍለዋል።
27እርሱም በሰዎች ፊት እንዲህ ብሎ ይዘምራል፤
‘እኔ ኃጢአት ሠርቻለሁ፤
የቀናውንም ነገር አጣምሜአለሁ፤
እግዚአብሔር ግን በደሌን አልቈጠረብኝም።
28ወደ ሙታን ዓለም ከመውረድም አዳነኝ፤
እነሆ፥ አሁን በሕይወት ተገኝቼ ብርሃንን አያለሁ።’
29“እነሆ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ነገር
ለሰዎች መላልሶ ያደርጋል።
30የሕይወትን ብርሃን እንዲያይ፥
ነፍሱን ከመቃብር ይመልሰዋል።
31“ኢዮብ ሆይ! የምነግርህን በጥንቃቄ አድምጥ፤
እስቲ አንተ ዝም በልና እኔ ልናገር።
32የምትለው ነገር ካለህ መልስልኝ፤
እኔ አንተን ነጻ ለማውጣት ስለምፈልግ ተናገር።
33አለበለዚያ ዝም ብለህ እኔ የምናገረውን ስማ፤
እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ