የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 32

32
የኤሊሁ ንግግር
(32፥1—37፥24)
1ኢዮብ “እኔ ጻድቅ ሰው ነኝ” ብሎ በሐሳቡ ስለጸና፥ ሦስቱ ሰዎች ንግግራቸውን አቆሙ። 2የራም ቤተሰብ የነበረው ቡዛዊው የባራኬል ልጅ ኤሊሁ ኢዮብ ራሱን ከእግዚአብሔር አብልጦ ጻድቅ ስላደረገ ተቈጣ። 3በኢዮብ ላይ የሚያስፈርድ በቂ መልስ ባለመስጠታቸው፥ ኤሊሁ በሦስቱ ጓደኞቹም ላይ ተቈጥቶ ነበር። 4ኤሊሁ በዕድሜ ከሌሎቹ ያነሰ በመሆኑ ሁሉም ተናግረው እስከሚጨርሱ ድረስ በተራው ከኢዮብ ጋር ለመናገር ይጠባበቅ ነበር። 5ሦስቱ ሰዎች ለኢዮብ አጥጋቢ መልስ ለመስጠት አለመቻላቸውን በማየቱ እጅግ ተቈጣ። 6ቡዛዊው የባራኪ ልጅ ኤሊሁ እንዲህ ሲል መለሰ፦
“እኔ በዕድሜዬ ከእናንተ ያነስኩ በመሆኔና
እናንተም አዛውንት በመሆናችሁ፥
ኀፍረትና ፍርሀት ተሰምቶኝ
ሐሳቤን ሳልገልጥ እስከ አሁን ቈይቼ ነበር።
7‘ሽማግሌዎች በቅድሚያ ይናገሩ፤
በረጅም ዕድሜ ያገኙትን ጥበብ ያስተምሩ’ ብዬ ነበር።
8ነገር ግን በሰው ዐድሮ ጥበብን የሚሰጥ
የልዑል እግዚአብሔር መንፈስ ነው።
9ሰዎችን ጠቢባን የሚያደርጋቸው ሽምግልና አይደለም፤
ትክክለኛውንም ነገር ለማስተዋል የሚረዳቸው የዕድሜ ብዛት አይደለም።
10ስለዚህ እኔም ሐሳቤን ልግለጥላችሁ፤
እናንተም በጥሞና አድምጡኝ።
11“እናንተ የምታቀርቡትን ምክንያት እጠባበቅ ነበር።
ሐሳባችሁን ግልጥ ለማድረግ ቃላት በመምረጥ፥
የምትናገሩትንም አዳምጥ ነበር።
12በጥንቃቄ አደመጥኳችሁ፤
ሆኖም፥ ማንም ኢዮብን ለማስተባበል የቻለ የለም፤
ከእናንተም መካከል ለእርሱ ንግግር አጥጋቢ መልስ የሰጠ የለም።
13ለኢዮብ ተገቢ መልስ ሊሰጠው የሚችል
እግዚአብሔር እንጂ ሰው ስላልሆነ፥
እናንተ ጥበብን አግኝተናል ብላችሁ በከንቱ አትመኩ።
14ኢዮብ የተከራከረው ከእናንተ ጋር እንጂ ከእኔ ጋር አልነበረም፤
እኔም በእናንተ አነጋገር ዐይነት አልመልስለትም።
15“እነርሱም ደንግጠው
የሚናገሩት ነገር ስላልነበራቸው
ምንም መናገር አልቻሉም።
16እነሆ! እነርሱ የሚናገሩትን አጥተው ዝም ብለው ቆመዋል፤
ታዲያ፥ እነርሱ ጸጥ ቢሉ፥
እኔም በትዕግሥት መጠባበቅ ይገባኛልን?
17አይሆንም! እኔም የበኩሌን መልስ እሰጣለሁ፤
አስተያየቴንም እገልጣለሁ።
18ብዙ የምናገረው ነገር ስላለኝ፥
ከእንግዲህ ወዲህ ዝም ማለት አልችልም።
19ሆዴ ሊፈነዳ እንደ ተቃረበ
እንደ አዲስ የወይን አቊማዳ ሆዴ ተነፍቶአል።
20ተናግሬ ይውጣልኝ፤
በአንደበቴ መልስ መስጠት አለብኝ።
21በዚህ ጉዳይ ለማንም አላደላም፤
ማንንም አላቆላምጥም።
22እኔ ሰውን ማቈላመጥ አይሆንልኝም፤
ይህንንም ባደርግ ፈጣሪዬ በፍጥነት ይቀጣኝ ነበር።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ