መጽሐፈ ኢዮብ 34
34
1ኤሊሁም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦
2“እናንተ ጠቢባን የምናገረውን ስሙኝ፤
እናንተም ዐዋቂዎች አድምጡኝ።
3የምግብ ጣዕም በምላስ እንደሚታወቅ፥
ንግግርም በጆሮ ይለያል። #ኢዮብ 12፥11።
4ትክክለኛ የሆነውን ነገር መርምረን እንወቅ፤
መልካሙንም ነገር አብረን እንማር።
5ኢዮብ ‘እኔ ንጹሕ ነኝ፤
እግዚአብሔር ግን ፍትሕ ነፈገኝ።
6እኔ እውነተኛ ስሆን፥ እንደ ውሸተኛ ተቈጠርኩ፤
ምንም በደል ሳይኖርብኝ በማይፈወስ ቊስል
እሠቃያለሁ’ ብሎአል።
7“እንደ ኢዮብ በእግዚአብሔር ላይ የሚያፌዝ ሰው ከቶ ይገኛልን?
8ጓደኞቹ ክፉ አድራጊዎች ናቸው፤
የሚውለውም ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነው።
9‘እግዚአብሔርን ማስደሰት፥
ለሰው ምንም አይጠቅመውም’ ይላል።
10“አስተዋዮች የሆናችሁ ሰዎች አድምጡኝ!
ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር፥
ስሕተትንም ማድረግ ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ!
11እግዚአብሔር ለሰው እንደ ሥራው ይከፍለዋል፤
በአካሄዱም መጠን የሚገባውን ያደርግለታል። #መዝ. 62፥12።
12ሁሉን የሚችል አምላክ ከቶ ክፉ ነገር አያደርግም፤
በማንኛውም ሰው ላይ ፍርድን አያዛባም።
13ምድርን ለእግዚአብሔር ዐደራ የሰጠው የለም፤
በዓለም ላይ ኀላፊ አድርጎ የሾመው የለም።
14እግዚአብሔር መንፈሱንና እስትንፋሱን
ወደ ራሱ ለመመለስ ቢያስብ፥
15የሰው ዘር ሁሉ በአንድነት በጠፋ ነበር፤
ወደ ዐፈርም በተመለሰ ነበር።
16አስተዋይ ብትሆን ይህን ስማ፤
ንግግሬንም አድምጥ።
17ፍትሕን የሚጠላ መግዛት ይችላልን?
ጻድቁንና ኀያሉን እግዚአብሔር በደለኛ ታደርገዋለህን?
18ንጉሡን የማትጠቅም ነህ፤
መኳንንቱንም ክፉዎች ናችሁ፤
የሚላቸው ማነው?
19ሁሉም የእጁ ሥራዎች ስለ ሆኑ፤
እርሱ ለመኳንንቱ አያደላም
ባለጸጋውን ከድኻው አይለይም።
20ሰዎች በእኩለ ሌሊት በቅጽበት ሊሞቱ ይችላሉ።
ተንቀጥቅጠውም ያልፋሉ።
ኀያላንም የማንም ሰው እጅ ሳይነካቸው ይወገዳሉ።
21እግዚአብሔር የሰዎችን ሁሉ እርምጃ ይመለከታል።
የእያንዳንዳቸውን እርምጃ ይቈጣጠራል።
22ክፉ አድራጊዎች የሚደበቁበት፤
ድቅድቅ ጨለማ ከቶ የለም።
23በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ ለመቅረብ
ቀጠሮ አይሰጣቸውም።
24ገዢዎችን ከሥልጣናቸው አውርዶ፥
በቦታቸው ሌሎችን ለመተካት፥
ምርመራ አያስፈልገውም።
25ስለዚህም ሥራቸውን ዐውቆ፥
በአንድ ሌሊት ከሥልጣናቸው አስወግዶ ያጠፋቸዋል።
26በሠሩት ዐመፃ ምክንያት
ኃጢአተኞችን በሰው ፊት ይቀጣቸዋል።
27ይህንንም የሚያደርግባቸው፥
እርሱን መከተል ስለ ተዉና
ትእዛዞቹንም ስለ ናቁ ነው።
28ድኾችን በመጨቈን ወደ እግዚአብሔር እንዲጮኹ አድርገዋቸዋል፤
እግዚአብሔርም የድኾችን ጩኸት ሰምቶአል።
29-30“እግዚአብሔርን የሚክድና
ሕዝቡን የሚያጠምድ ንጉሥ ሲነግሥ፥
እግዚአብሔር ዝም ቢል፥
ወይም ፊቱን ቢሰውር ማን ሊወቅሰው ይችላል?
31“ምናልባት አንድ ሰው ለእግዚአብሔር ‘እስከ አሁን
በድዬአለሁ ዳግመኛ አልበድልም፥
32የሠራሁት ኃጢአት የትኛው እንደ ሆነ አስተምረኝ፤
በድዬም ከሆነ፥ ዳግመኛ አልሠራም’ ያለው ሰው አለን?
33ታዲያ፥ አንተ ንስሓ መግባት እንቢ እያልክ፥
አንተ በምታቀርበው ሐሳብ መሠረት
እግዚአብሔር ምኞትህን እንዲፈጽምልህ ትፈልጋለህን?
34“የሚሰሙኝ ሰዎች እንዲህ ይሉኛል፤
የሚያስተውሉ ሰዎች እንዲህ ይላሉ፦
35‘ኢዮብ የሚናገረው ያለ ዕውቀት ነው፤
ንግግሩም ፍሬ ቢስ ነው’
36የክፉዎች ሰዎችን የመሰለ መልስ ስለሚሰጥ
ምነው ኢዮብ እስከ መጨረሻው ድረስ በተፈተነ!
37በመካከላችን ሕገ ወጥ በመሆን፥
በእግዚአብሔር ላይ ንቀትን በማብዛት
ኢዮብ በኃጢአቱ ላይ ዐመፅን ጨምሮአል።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 34: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997