የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 31

31
1“ቈንጆይቱን በፍትወት ዐይን እንዳልመለከት፥
ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቼአለሁ።
2“ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ
የተወሰነው የሰው ዕድል ፈንታ ምንድን ነው?
በአርያም ካለው ሁሉን ከሚችል አምላክ፥
የተሰጠው ድርሻስ ምንድን ነው?
3በክፉ ሰው ላይ መዓት፥
በበደለኛ ሰውም ላይ ጥፋት፥
የታወቀ አይደለምን?
4እግዚአብሔር የማደርገውን ሁሉ አያይምን?
እርምጃዎቼንስ አይቈጣጠርምን?
5“ሐሰት ተናግሬ እንደ ሆነ፥
ሰውንም አታልዬ እንደ ሆነ፥
6እግዚአብሔር በትክክለኛ ሚዛን ይመዝነኝ፤
በቅንነት መጽናቴንም ይወቅ።
7ከትክክለኛው መንገድ ወጥቼ እንደ ሆነ፥
ዐይኔ ያየውን ሁሉ ልቤ ጐምጅቶ እንደ ሆነ፤
እጄም በኃጢአት አድፎ እንደ ሆነ፥
8እኔ የዘራሁትን ሌላ ሰው ይብላው፤
ቡቃያዬም ሁሉ ተነቃቅሎ ይጥፋ።
9ልቤ በሌላ ሴት ፍቅር ተማርኮ እንደ ሆነ፥
የጐረቤቴንም ሚስት ለማግኘት በደጃፉ አድብቼ እንደ ሆነ፥
10ሚስቴ ለሌላ ሰው ፈጫይ ሆና ታገልግል፤
መኝታዋም ከሌሎች ወንዶች ጋር ይሁን።
11ይህም ተግባር በሕግ ፊት የሚያስቀጣ፥
ታላቅ ወንጀል ነው።
12ይህ ኃጢአት እንደ እሳት አቃጥሎ የሚያጠፋ ስለ ሆነ
እኔ ይህን ብሠራ ኖሮ ሀብቴን ሁሉ ባወደመው ነበር።
13“ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቼ አቤቱታ አቅርበውልኝ
አቤቱታቸውን ሳልቀበል ቀርቼ እንደ ሆነ፥
14በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ በቆምኩ ጊዜ
ምን ይበጀኝ ይሆን?
በፍርድ በሚመረምረኝስ ጊዜ ለሚያቀርብልኝ ጥያቄ
ምን መልስ መስጠት እችል ይሆን?
15በማሕፀን ውስጥ እኔን የፈጠረ
አገልጋዮቼንስ የፈጠረ አይደለምን?
ሁላችንንስ በማሕፀን ውስጥ የሠራ፥
እርሱ አይደለምን?
16“ድኾች የሚለምኑትን ከልክዬ አላውቅም፤
ባሎቻቸው የሞቱባቸውንም ሴቶች ከማጽናናት አልተቈጠብኩም።
17የሙት ልጆች እየራባቸው
ምግቤን ብቻዬን አልበላሁም።
18ነገር ግን ከወጣትነቴ ጀምሬ እንደ አባት ሆኜላቸዋለሁ፤
በሕይወቴ ዘመኔ ሁሉ ባልዋ የሞተባትን ረድቼአለሁ።
19አንድ ሰው ከልብስ እጦት ወይም አንድ ችግረኛ
የሚለብሰው አጥቶ ራቁቱን ሆኖ ባይ፥
20ከበጎቼ ጠጒር የተሠራ ልብስ አልብሼው
ሞቆት ሳይመርቀኝ የቀረበት ጊዜ የለም።
21በፍርድ ሸንጎ ተሰሚነት ያለኝ መሆኔን በማወቄ
በሙት ልጅ ላይ እጄን አንሥቼ አላውቅም።
22ይህን ሁሉ ሳላደርግ ቀርቼ ከሆነ ክንዴ ከትከሻዬ ይውለቅ፤
ከመገናኛውም ተሰብሮ ይለይ፥
23የእግዚአብሔርን መቅሠፍት እፈራለሁ፤
ከግርማውም አስፈሪነት የተነሣ በፊቱ መቆም አልችልም።
24“እምነቴን በሀብት ላይ አድርጌ አላውቅም፤
ወይም ንጹሕ ወርቅንም መታመኛዬ አላደረግሁም።
25‘ሀብቴ በዝቷል፥
በብልጽግናዬም ብዙ ገንዘብ አግኝቼአለሁ’ ብዬ ተደስቼ አላውቅም።
26የፀሐይን ማሸብረቅ፥
የጨረቃን መድመቅ ተመልክቼ፥
27ልቤ በስውር ለእነርሱ አልተማረከም
እጄንም ዘርግቼ በመሳም አክብሮት አላቀረብኩላቸውም።
28ይህን ማድረግ በላይ ለሚገኘው አምላክ እምነተቢስነት ስለ ሆነ፥
እነዚህ ድርጊቶች የሞት ፍርድ የሚያመጡ ኃጢአቶች ናቸው።
29“በሚጠሉኝ ሰዎች ውድቀት አልተደሰትኩም፤
ክፉ ነገርም ሲደርስባቸው ሐሴት አላደረግሁም
30‘ጠላቶቼ ይጥፉ’ ብዬ በመራገም
ኃጢአት ከቶ አልሠራሁም።
31በእርግጥ ቤተሰቦቼ ‘ከእርሱ ዘንድ
ምግብ በልቶ ያልጠገበ ከቶ ማነው?’ ብለው ይመሰክራሉ።
32ቤቴን ለመንገደኞች ክፍት አደርግ ስለ ነበረ፥
በውጪ የሚያድር እንግዳ ከቶ አልነበረም።
33“በደሌን በውስጤ አልሸሸግሁም
እንደ ሌሎች ሰዎች ኃጢአቴንም አልሰወርኩም።
34የሕዝቡ ብዛት አስፈርቶኝና፥
የቤተሰብም ነቀፋ አስደንግጦኝ
ጸጥ ብዬ በቤት ውስጥ የተደበቅኹበት ጊዜ የለም።
35“ምነው የሚሰማኝ ባገኘሁ!
መከላከያዬን አቀርባለሁ፤
ሁሉን ቻይ አምላክ ይመልስልኝ!
ምነው ከሳሼም የክሱን ዝርዝር በጽሑፍ አቅርቦልኝ ባየሁት!
36እንደ ሽልማት ምልክት በደረቴ ላይ አደርጋቸው ነበር።
እንደ አክሊልም በራሴ ላይ ባስቀመጥኳቸው ነበር።
37ሥልጣን እንዳለው ሰው በእግዚአብሔር ፊት በድፍረት ቆሜ፥
ያደረግኹትን ሁሉ በዝርዝር በገለጥኩለት ነበር።
38“ሕጋዊ ባለርስቶችን ጨቊኜ
ርስታቸውንም ነጥቄ አርሼ እንደ ሆነ
39የባለርስቶችን መንፈስ አሳዝኜ
ምንም ሳልከፍል ምርቱን ሁሉ
በልቼው እንደ ሆነ።
40በዚያች መሬት ላይ በስንዴ ፈንታ እሾኽ፥
በገብስ ፈንታ አረም ይብቀል።”
የኢዮብ ንግግር እዚህ ላይ ተፈጸመ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ