መጽሐፈ ኢዮብ 30
30
1“አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ ያነሱ ሰዎች ያፌዙብኛል፤
የእነርሱ አባቶች የበጎቼን መንጋ ከሚጠብቁ
ውሾቼ ጋር እንኳ እንዲሰማሩ የምንቃቸው ሰዎች ነበሩ።
2ኀይላቸው የደከመ ስለ ነበረ፥
ለእኔ ምንም አይጠቅሙኝም ነበር።
3ከችግርና ከራብ ብዛት የተነሣ፥
ወደ በረሓ እየሄዱ
ሥራ ሥሮችን ያኝኩ ነበር።
4ጨው ጨው የሚሉ የበረሓ ቅጠላ ቅጠሎችን ይለቅሙ ነበር፤
ጣዕም የሌላቸውንም የክትክታ ሥሮች ይበሉ ነበር።
5ሰዎች ሌቦችን እየጮኹ እንደሚያባርሩ፥
እነርሱንም ከኅብረተሰቡ መካከል ያባርሩአቸው ነበር፤
6መኖሪያቸውንም በየዋሻውና
በየገደሉ ሥር በተቈፈሩ ጒድጓዶች ውስጥ ለማድረግ ተገደዱ።
7በየጫካው እየዞሩ እንደ ዱር አውሬ ይጮኹ ነበር፤
በየቊጥቋጦውም ሥር ተሰባስበው ይኖሩ ነበር።
8በጅራፍ እየተገረፉ ከአገር በመባረራቸው፥
ስማቸው የጠፋ አእምሮ ቢሶች ሆነው ይኖሩ ነበር።
9“አሁን ልጆቻቸው በዘፈን ያፌዙብኛል፤
በመካከላቸውም የመሳለቂያ ርእስ ሆኛለሁ።
10ተጸይፈውኝ ከእኔ ይርቃሉ፤
ያለ አንዳች ኀፍረት በፊቴ ምራቃቸውን ይተፋሉ።
11እግዚአብሔር ኀይሌን አድክሞ ስላዋረደኝ፥
እነርሱ ልጓሙ እንደ ወለቀለት ፈረስ እንዳሻቸው ፈነጩብኝ።
12በስተቀኜ በኩል ስድ ዐደጎች ተነሡብኝ፤
እግሬንም ለማሰናከል ወጥመድ አጠመዱ፤
በእኔም ላይ ከበባ አደረጉ።
13መተላለፊያ መንገዴን ዘግተው
ሊያጠፉኝ ይፈልጋሉ፤
ይህን ከማድረግ የሚገታቸው የለም። #30፥13 ከማድረግ የሚገታቸው፦ ወይም ለማድረግ የሚረዳቸው።
14ጐርፍ ጥሶ እንደሚገባ መከላከያዬን ጥሰው ገቡ፤
ሁሉንም እየሰባበሩ በእኔ ላይ መጡ።
15ታላቅ ድንጋጤ ይዞኛል፤
ክብሬ እንደ ነፋስ ሽውታ አልፎአል፤
የመዳኔም ተስፋ እንደ ጉም በኖ ጠፍቶአል።
16“ነፍሴ እጅግ ተጨነቀች
ለሞትም ተቃርቤአለሁ።
17ሌሊቱን ሙሉ አጥንቶቼ በሕመም ይሠቃያሉ፤
ሕመሙም ዕረፍት አይሰጠኝም።
18ከሕመሜ ጽናት የተነሣ
ልብሴ ተቈራፍዶ ተበላሽቶአል፤
እንደ ሸሚዝ ክሳድ አንቆ ይዞኛል።
19እግዚአብሔር ዐፈር ላይ ወርውሮ ስለ ጣለኝ፥
ትቢያና ዐመድ መስያለሁ።
20“እግዚአብሔር ሆይ! አንተን ለመንኩ፤
ነገር ግን አልመለስክልኝም፤
ቆሜም ወደ አንተ ጸለይኩ፤ አንተ ግን ፊትህን አልመለስክልኝም።
21እጅግ ጨከንክብኝ፤
በታላቅ ኀይልህም አሳደድከኝ።
22አንሥተህ በነፋስ ላይ አስቀመጥከኝ፥ እንዲያዞረኝም አደረግህ፤
ዐውሎ ነፋሱም ያንገዋልለኛል።
23የሰው ሁሉ ዕድል ፈንታ ለሆነው ለሞት አሳልፈህ
እንደምትሰጠኝ ዐውቃለሁ።
24አንድ የተቸገረ ሰው ለእርዳታ እጁን ዘርግቶ ሲጮኽ
በእርግጥ ማንም ሰው አያጠቃውም።
25ለተቸገሩ ሰዎች አላለቀስኩምን?
ለድኾችስ አልተጨነቅኹምን?
26መልካም ነገር አገኛለሁ ብዬ ስመኝ፥
ክፉ ነገር ደረሰብኝ፤
ብርሃን ይወጣልኛል ብዬ ስጠባበቅ፥
ቀኑ ጨለመብኝ።
27ልቤ ተጨነቀች፤ ምንም ሰላም አላገኘሁም፤
የመከራ ቀኖችም ደረሱብኝ።
28ሰውነቴ በፀሐይ ቃጠሎ ሳይሆን በሐዘን ጠቈረ፤
በአደባባይም መካከል ቆሜ ርዳታ እጠይቃለሁ።
29ከሰው ተለይቼ ለቀበሮ ወንድም
ለሰጎንም ባልንጀራ ሆንኩ።
30ቆዳዬ ጠቊሮ ተገለፈፈ፤
ሰውነቴም በትኩሳት ተቃጠለ።
31ደስታዬን እገልጥባቸው የነበሩት በገና እና እምቢልታ
አሁን የሐዘን እንጒርጒሮዬ ማሰሚያ ሆነዋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 30: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997