መጽሐፈ ኢዮብ 29
29
የኢዮብ የመጨረሻ ስሞታ
1ኢዮብም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦
2“የአሁኑ ኑሮዬ ቀድሞ እግዚአብሔር
ይጠብቀኝ እንደ ነበረው ጊዜ ቢሆንልኝ
እንዴት ደስ ባለኝ ነበር!
3ያን ጊዜ በጨለማ ውስጥ ስሄድ፥
እግዚአብሔር መብራቱን እያበራልኝ
በብርሃን እራመድ ነበር።
4ምነው የእግዚአብሔር ረድኤት ቤቴን ይጠብቅ
እንደ ነበረበት እንደ ወጣትነቴ
ጊዜ በሆንኩ!
5ሁሉን የሚችል አምላክ ገና ስላልተለየኝ፥
ልጆቼ ሁሉ በዙሪያዬ ነበሩ።
6እግሮቼ እንኳ በወተት እስኪታጠቡ ድረስ ብዙ ወተት አገኝ ነበር።
የወይራ ዛፎቼም በጭንጫ መሬት ላይ እንኳ ተተክለው
እንደ ጐርፍ የሚወርድ ብዙ ዘይት ይሰጡኝ ነበር።
7ወደ ከተማም አደባባይ እየሄድኩ
በሸንጎ እቀመጥ በነበረ ጊዜ፥
8ወጣቶች እኔን ሲያዩ በአክብሮት ከፊቴ ገለል ይሉ ነበር፤
ሽማግሌዎችም ስለ እኔ ክብር ከተቀመጡበት ይነሡ ነበር።
9ሲነጋገሩ የነበሩ የሕዝብ መሪዎችም
እኔን ሲያዩ እጆቻቸውን በአፋቸው ላይ አድርገው ጸጥ ይሉ ነበር።
10የአገር መኳንንትም እኔ ባለሁበት ጸጥ ይሉ ነበር፤
ምላሳቸው ተሳስሮ መናገር ያቅታቸው ነበር።
11“የሰማኝ ሁሉ አሞገሰኝ፤
ያየኝ ሁሉ አመሰገነኝ።
12ይህም የሆነው የድኾችን ጩኸት ሰምቼ እታደጋቸውና፥
ወላጆቻቸው የሞቱባቸውንም ልጆች እረዳቸው ስለ ነበረ ነው።
13ለሞት የተቃረቡትን ሰዎች ስለምረዳ መረቁኝ፤
ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ስለምረዳቸው በደስታ ይዘምሩ ነበር።
14ጽድቅን እንደ ልብስ ለበስኳት፤
ትክክለኛ ፍርድንም እንደ ካባ ደረብኳት፤ እንደ ቆብም ደፋኋት።
15ለዕውሮች ዐይን፥
ለአንካሶችም እግር ነበርኩ።
16ለድኾች አባት፥
ለማላውቃቸውም ሰዎች ጠበቃ ነበርኩ።
17የግፈኛውን መንጋጋ ሰበርኩ፤
ነጥቆ የወሰደውንም ከአፉ አስጣልኩ።
18“ ‘ዕድሜዬ እንደ አሸዋ በዝቶ፥
በቤቴ እንዳለሁ በክብር እሞታለሁ’ ብዬ ነበር።
19ሥሮቹ ዘወትር ውሃ እንደሚያገኙና
ቅርንጫፎቹም በጠል እንደሚርሱ ዛፍ ነበርኩ።
20ሁልጊዜ እንደ ተከበርኩ እኖር ነበር
ኀይሌም ዘወትር ይታደስ ነበር።
21ሰዎች እኔን በማዳመጥ ጸጥ ይሉ ነበር፤
ምክሬንም ለመስማት በዝምታ ያዳምጡ ነበር።
22ንግግሬ ያረካቸው ስለ ነበር፥
ከእኔ ንግግር በኋላ የሚናገር ሰው አልነበረም።
23ገበሬ የበልግ ዝናብ ለማግኘት እንደሚመኝ፤
እነርሱም የኔን ንግግር ለመስማት
አፋቸውን ከፍተው ይጠባበቁ ነበር።
24ፈገግ ስልላቸው ተዝናኑ፤
ፊቴ ሲበራ የተቋጠረ ፊታቸው ተፍታታ።
25እኔ እንደ ፈለግኹት አስተዳድራቸው ነበር፤
ሠራዊቱንም እንደሚመራ ንጉሥ እመራቸው ነበር፤
በሚያዝኑበትም ጊዜ አጽናናቸው ነበር።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 29: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997