መጽሐፈ ኢዮብ 22
22
1ቴማናዊውም ኤሊፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፦
2“ሰው እግዚአብሔርን ሊጠቅም ይችላልን?
ሌላው ቀርቶ ጠቢብ እንኳ ቢሆን ጥቅሙ ለራሱ እንጂ
ለእግዚአብሔር አይሆንም።
3የአንተ መልካም ሥራ ሁሉን ለሚችል አምላክ ምን ይጠቅመዋል?
የኑሮህስ ፍጹምነት ለእርሱ ምን ይረባዋል? #ኢዮብ 35፥6-8።
4ታዲያ፥ በአንተ ላይ የፈረደብህና
እንዲህ አድርጎ የገሠጸህ
የእግዚአብሔር ወዳጅ ስለ ሆንክ ነውን?
5ይህ ሁሉ የደረሰብህ ክፋትህ ስለ በዛና
ኃጢአትህም ወሰን የሌለው ስለ ሆነ አይደለምን?
6ወንድሞችህን ያለ አንዳች ምክንያት በዋስትና አስይዘሃቸዋል፤
ሌሎችንም ልብሳቸውን ገፈህ ራቊታቸውን አስቀርተሃቸዋል።
7ተርበውና ተጠምተው ለደከሙ
እህልና ውሃ ከልክለሃል።
8ምድር የኀይለኛ ሰዎች ንብረት፥
የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ይዞታ ሆናለች።
9ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ባዶ እጃቸውን ሰደሃል፤
የሙት ልጆችንም መተዳደሪያ አጥፍተሃል።
10በዚህም ምክንያት እነሆ፥ ዙሪያህን በወጥመድ ተከበሃል፤
ድንገተኛ አደጋም ያሸብርሃል፤
11ማየት እስከሚሳንህ ድረስ ጨለማ ወርሶሃል፤
የጐርፍ ውሃም አጥለቅልቆሃል።
12“እግዚአብሔር ከፍ ባለው ሰማይ የሚኖር አይደለምን?
ከዋክብት ምንም እንኳ ከፍ ባለ ስፍራ ቢሆኑ፥
እርሱ ከበላያቸው ሆኖ ይመለከታቸዋል።
13አንተ ግን ‘እግዚአብሔር ምን ያውቃል?
ከድቅድቅ ጨለማ ባሻገር ሆኖ
እንዴት ሊፈርድብን ይችላል?
14ጠፈር ላይ ሲመላለስ
ድቅድቅ ደመና ስለሚጋርደው
ሊያይ አይችልም’ ትላለህ።
15“ኃጢአተኞች ይመላለሱበት የነበረው
የዱሮውን መንገድ ትከተላለህን?
16እነርሱ እኮ ጊዜአቸው ሳይደርስ ተቀሥፈዋል፤
በጐርፍም ተጠራርገው ሥር መሠረታቸው ጠፍቶአል።
17እነርሱም ሁሉን የሚችለውን አምላክ፦ ‘ከእኛ ራቅ፤ ምን
ልታደርግልን ትችላለህ?’ አሉት።
18ሆኖም ቤታቸውን በብልጽግና የሞላው እግዚአብሔር ነው።
ስለዚህ እኔ የክፉ ሰዎችን ሐሳብ አልቀበልም።
19ክፉ ሰዎች ሲቀጡ በማየት
ደጋግ ሰዎች ይደሰታሉ፤
ቀጥተኞች እንዲህ እያሉ በእነርሱ ላይ ያፌዛሉ፥
20‘በእርግጥ ጠላቶቻችን ጠፍተዋል፤
ንብረታቸውም ሁሉ በእሳት ጋይቶአል።’
21“ስለዚህ ኢዮብ ሆይ፥ ራስህን ለእግዚአብሔር አስገዛ፤
ከእርሱም ጋር ሰላም ይኑርህ፤
ይህን ብታደርግ መልካም ነገርን ታገኛለህ።
22እግዚአብሔር የሚሰጥህን ትምህርት ተቀበል፤
ቃሉንም በልብህ አኑር።
23ራስህን ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመልስ
እንደ ቀድሞህ ትሆናለህ።
ከቤትህ የክፋትን ሥራ አስወግድ
24ወርቅን ወደ ትቢያ ጣለው፤
የኦፊርንም ወርቅ እንደ ጅረት ድንጋይ ወርውረው፤
25በዚያን ጊዜ ሁሉን ቻይ አምላክ ለአንተ
ወርቅና ንጹሕ ብር ይሆንልሃል።
26በዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፤
በእርሱም ተማምነህ ትኖራለህ።
27ወደ እርሱም በምትጸልይበት ጊዜ
የለመንከውን ሁሉ ስለሚፈጽምልህ፥
ስለትህን ትከፍላለህ።
28ዕቅድህ ሁሉ ይሳካልሃል፤
መንገድህ ሁሉ ብርሃን ይሆንልሃል።
29እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ያዋርዳል፤
ትሑታንን ግን ያድናቸዋል።
30አንተም ቅን ልብ ያለህ ብትሆን
እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፤
እጆችህም ከበደል ሥራ የነጹ ቢሆኑ
እግዚአብሔር ይታደግሃል።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 22: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997