መጽሐፈ ኢዮብ 1
1
ሰይጣን ኢዮብን መፈተኑ
1ዑፅ ተብላ በምትጠራ አገር ኢዮብ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ከክፉ ነገር ሁሉ ርቆ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ምንም ነውር የሌለበት፥ ቅን ሰው ነበር። 2ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆችም ነበሩት።
3በሀብትም በኩል ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህ ግመሎች፥ አምስት መቶ ጥማድ በሬዎችና አምስት መቶ አህዮች ነበሩት፤ እንዲሁም እጅግ ብዙ አገልጋዮች ነበሩት፤ በምሥራቅ አገር ካሉት ሰዎች ሁሉ እርሱን የሚያኽል ሀብታምና ታላቅ ሰው አልነበረም።
4የኢዮብ ወንዶች ልጆች በእያንዳንዳቸው ቤት በተራ ግብዣ እያዘጋጁ በአንድነት ተሰብስበው ይደሰቱ ነበር፤ ሦስቱንም እኅቶቻቸውን እያስጠሩ ከእነርሱ ጋር አብረው ይበሉና ይጠጡ ነበር። 5የግብዣዎቹ ቀኖች ከተፈጸሙ በኋላ ኢዮብ በማለዳ ተነሥቶ ልጆቹን ያስጠራና በእያንዳንዱ ልጁ ስም መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ ይህንንም የሚያደርገው “ምናልባት ከልጆቼ አንዱ እግዚአብሔርን በመስደብ በድሎ ይሆናል!” በሚል ስጋት ልጆቹን ከኃጢአት ለማንጻት ነበር። ኢዮብ ይህን ሥርዓት ሳያቋርጥ ዘወትር ይፈጽም ነበር።
6ከዕለታት አንድ ቀን የሰማይ መላእክት በእግዚአብሔር ፊት በቀረቡ ጊዜ ሰይጣንም አብሮአቸው ቀረበ። #ዘፍ. 6፥2። 7እግዚአብሔርም “ከወዴት መጣህ?” ብሎ ሰይጣንን ጠየቀው።
ሰይጣንም “በምድር ዙሪያ ወዲያና ወዲህ እመላለስ ነበር” አለ።
8እግዚአብሔር ሰይጣንን “አገልጋዬን ኢዮብን ልብ ብለህ አየኸውን? እርሱን የመሰለ ታማኝና ደግ ሰው በምድር ላይ አይገኝም፤ እርሱ ከክፋት ሁሉ ርቆ እኔን የሚፈራ ቀጥተኛ ሰው ነው” አለ።
9ሰይጣንም እንዲህ አለ፦ “ኢዮብ አንተን እግዚአብሔርን የሚፈራ ያለ ምክንያት ነውን? 10እርሱ አንተን የሚፈራህ እርሱንና ልጆቹን፥ ያለውንም ንብረት ሁሉ በደኅና ስለ ጠበቅህለት፥ የሚሠራውንም ሁሉ ስለ ባረክህለትና ብዙ የከብት መንጋ ስለ ሰጠኸው አይደለምን? 11ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ብታጠፋበት ፊት ለፊት ይሰድብሃል።” #ራዕ. 12፥10።
12እግዚአብሔርም ሰይጣንን “እሺ፤ እንግዲያውስ በኢዮብ ላይ ብቻ አንዳች ጒዳት አታድርስበት እንጂ ባለው ሀብት ሁሉ ላይ የፈለግኸውን ማድረግ ትችላለህ” አለው። ከዚህ በኋላ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ።
የኢዮብ ልጆች መሞትና፤ ሀብቱም ሁሉ መጥፋቱ
13ከዕለታት አንድ ቀን የኢዮብ ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ተሰብስበው እየበሉና የወይን ጠጅ እየጠጡ ይደሰቱ ነበር። 14በዚያኑ ዕለት አንድ መልእክተኛ ወደ ኢዮብ መጥቶ እንዲህ አለ፦ “በሬዎች ጠምደን እናርስ ነበር፤ አህዮችም በአጠገባችን ባለው መስክ ተሰማርተው ነበር፤ 15የሳባ ሰዎች መጥተው አደጋ በመጣል ሁሉንም ዘርፈው ወሰዱ፤ አገልጋዮችህን ሁሉ በሰይፍ ገደሉአቸው፤ እኔ ብቻ አምልጬ የሆነውን ነገር ልነግርህ መጣሁ።”
16የመጀመሪያው መልእክተኛ ንግግሩን ገና ሳይጨርስ ሌላ መልእክተኛ መጣና “በጎቹንና እረኞቹን በሙሉ መብረቅ ከሰማይ ወርዶ ገደላቸው፤ እኔ ብቻ አምልጬ የሆነውን ነገር ልነግርህ መጣሁ” አለው።
17ይኸኛው መልእክተኛ ተናግሮ ሳይጨርስ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ፥ “በሦስት ቡድን የተከፈሉ የከለዳውያን ዘራፊዎች በድንገት አደጋ ጣሉብን፤ ግመሎቹን በሙሉ ወሰዱአቸው፤ አገልጋዮችህንም በሙሉ በሰይፍ ገደሉአቸው፤ እኔ ብቻ አምልጬ የሆነውን ነገር ልነግርህ መጣሁ” አለው።
18ይኸኛው መልእክተኛም ተናግሮ ሳይጨርስ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ “ልጆችህ በሙሉ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ተሰብስበው እየበሉና የወይን ጠጅ እየጠጡ ይደሰቱ ነበር፤ 19ከበረሓ የተነሣ ዐውሎ ነፋስ በድንገት መጥቶ ቤቱን በሙሉ በገለባበጠው ጊዜ ቤቱ በላያቸው ላይ ስለ ተደረመሰ ሞቱ፤ እኔ ብቻ አምልጬ የሆነውን ነገር ልነግርህ መጣሁ” አለው።
20ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢዮብ ተነሥቶ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ራሱን ተላጨ፤ በግምባሩም ወደ መሬት ተደፍቶ በመስገድ፥ 21“ከእናቴ ማሕፀን ራቁቴን ተወለድኩ፤ ስሞትም ራቁቴን እሄዳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ወሰደ፤ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን!” አለ።
22ኢዮብ ምንም እንኳ ይህ ሁሉ ፈተና ቢደርስበት ከቶ ኃጢአት አልሠራም፤ በእግዚአብሔርም ላይ አላማረረም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997