መጽሐፈ ኢዮብ መግቢያ
መግቢያ
በመጽሐፈ ኢዮብ የምናገኘው ታሪክ ብርቱ ሥቃይና ጥፋት ስለ ደረሰበት ስለ አንድ ደግ ሰው የሚገልጥ ነው። ይህ ሰው ልጆቹንና ንብረቱን ሁሉ ከማጣቱም ሌላ በብርቱ ቊስል ተመትቶ ይሠቃያል፤ ከዚህ በኋላ በቅኔ መልክ በቀረቡ ሦስት ውይይቶች ኢዮብና የኢዮብ ወዳጆች በዚህ አሠቃቂ ሁኔታ የተሰማቸውን ስሜት ይገልጣሉ፤ በመጨረሻም እግዚአብሔር ለኢዮብ ይገለጥለታል።
የኢዮብ ወዳጆችም በኢዮብ ላይ ስለ ደረሰው መከራ አስተያየት የሚሰጡት በተለመደው የሃይማኖት አስተሳሰብ ላይ ተመርኲዘው ነው፤ ስለዚህ እነርሱ “እግዚአብሔር ለደግ ሰው በጎ ዋጋ ሲሰጥ፥ ክፉውን ሰው ይቀጣል፤ በዚህ ዐይነት ኢዮብ ይህ ሁሉ መከራ የደረሰበት ኃጢአት በመሥራቱ ይሆናል” ይላሉ፤ ነገር ግን ኢዮብ ፍጹምና ደግ ሰው በመሆኑ ይህን የመሰለ ከባድ ቅጣት የሚገባው አልነበረም፤ እንዲያውም እንቆቅልሽ የሆነው ነገር እርሱን በመሰለ ደግ ሰው ላይ ይህን ያኽል ከባድ ቅጣት መድረሱ ነው፤ ምንም እንኳ ኢዮብ እምነቱ ባይናጋ፥ ትክክለኛውን ፍርድ በመስጠት ነጻ እንዲያወጣውና ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንዲመልሰው እግዚአብሔርን አጥብቆ ከመጠየቅ አልቦዘነም።
እግዚአብሔር ለኢዮብ ጥያቄዎች ሁሉ በዝርዝር መልስ የሰጠ ባይሆንም፥ የእምነቱን ጽናት በማድነቅ መለኮታዊ ኀይሉንና ጥበቡን አስደናቂ በሆነ የግጥም ሥነ ጽሑፍ አቀራረብ ገልጦታል፤ ከዚያም በኋላ ኢዮብ እግዚአብሔር ታላቅና ጠቢብ መሆኑን አረጋግጦ ድፍረትና ቊጣ የተሞሉባቸውን ቃላት በመናገሩ በመጸጸት ንስሓ ገብቶአል።
በመጨረሻ ላይ ግጥም ባልሆነ አጻጻፍ የተመለከተው ክፍል የሚያስረዳው ኢዮብ ወደ ቀድሞ ሁኔታው መመለሱንና እንዲያውም በንብረት በኩል ከድሮ የበለጠ ማግኘቱን ነው፤ የኢዮብ ወዳጆች በእርሱ ላይ የደረሰው መከራ በምን ምክንያት መሆኑ ስላልገባቸው እግዚአብሔር በብርቱ ገሥጾአቸዋል፤ ከልማዳዊ ሃይማኖት አስተሳሰብ ይልቅ እግዚአብሔር ታላቅ መሆኑን የተረዳ ኢዮብ ብቻ ነበር።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
ኢዮብ ሀብቱን፥ ቤተሰቡንና ጤንነቱን ማጣቱ 1፥10—2፥13
ኢዮብ የተወለደበትን ቀን መርገሙ 3፥1-26
የመጀመሪያው ዙር ውይይት 4፥1—14፥22
የሁለተኛው ዙር ውይይት 15፥1—21፥34
የሦስተኛው ዙር ውይይት 22፥1—26፥14
የኢዮብ የመጨረሻ ንግግር 27፥1—30፥31
ኢዮብ ጥፋት የሌለበት መሆኑን አረጋግጦ መናገሩ 31፥1-40
የኤሊሁ ንግግር 32፥1—37፥24
ለመጀመሪያው ጊዜ የእግዚአብሔር ንግግር 38፥1—39፥30
ለሁለተኛው ጊዜ የእግዚአብሔር ንግግርና የኢዮብ መልስ 40፥1—42፥6
እግዚአብሔር እንደገና ኢዮብን በጤንነት፥ በሀብትና በቤተሰብ እንደ ባረከው 42፥7-17
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ መግቢያ: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997