የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 2

2
ሰይጣን ኢዮብን እንደገና መፈተኑ
1ከዕለታት አንድ ቀን የሰማይ መላእክት በእግዚአብሔር ፊት በቀረቡ ጊዜ ሰይጣንም አብሮአቸው ቀረበ።
2እግዚአብሔርም “ከወዴት መጣህ?” ብሎ ሰይጣንን ጠየቀው። ሰይጣንም “በምድር ዙሪያ ወዲያና ወዲህ እመላለስ ነበር” አለው።
3እግዚአብሔርም ሰይጣንን “አገልጋዬን ኢዮብን ልብ ብለህ አየኸውን? እርሱን የመሰለ ታማኝና ደግ ሰው በምድር ላይ አይገኝም፤ እርሱ ከክፋት ሁሉ ርቆ እኔን የሚፈራ ቀጥተኛ ሰው ነው፤ እርሱን ማጥፋት እንድትችል እፈቅድልህ ዘንድ ያነሣሣኸኝ በከንቱ ነው፤ እነሆ፥ ኢዮብ አሁንም በቅንነቱ እንደ ጸና ነው” አለው።
4ሰይጣንም “በቊርበት ፈንታ ቊርበት” እንዲሉ፥ “ሰው እኮ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል። 5ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ በመላ ሰውነቱ ላይ ጒዳት ብታደርስበት በእርግጥ ፊት ለፊት ይሰድብሃል!” አለው።
6እግዚአብሔርም ሰይጣንን “መልካም ነው፤ አትግደለው እንጂ በእርሱ ላይ የፈለግኸውን ማድረግ ትችላለህ” አለው።
7ከዚህ በኋላ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ኢዮብን ከራስ ጠጒሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ በከባድ ቊስል እንዲሠቃይ አደረገው። #2፥7 በቊርበት ፈንታ ቊርበት፦ ብድር ወይም ውለታ መመላለስን የሚገልጥ ሐሳብ ነው። 8ከዚህም የተነሣ ኢዮብ በዐመድ ክምር ላይ ተቀምጦ ቊስሉን በገል ያክ ጀመር።
9ሚስቱም “አሁንም በእግዚአብሔር ላይ ያለህ ቅንነት እንደ ጸና ነውን? ይልቅስ እግዚአብሔርን ካደውና ሙት!” አለችው።
10ኢዮብም “እንዴት የሞኝ ሴት ንግግር ትናገሪያለሽ? እግዚአብሔር መልካም ነገር ሲሰጠን በደስታ እንቀበላለን፤ ታዲያ፥ መከራ ሲያመጣብን በእርሱ ላይ ማጒረምረም ይገባናልን?” አላት።
ኢዮብ ምንም እንኳ ይህ ሁሉ መከራና ሥቃይ ቢደርስበት በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ነገር በመናገር ኃጢአት አልሠራም።
ሦስት የኢዮብ ወዳጆች ሊጐበኙት መምጣታቸው
11የቴማን አገር ሰው የሆነው ኤሊፋዝ፥ የሹሐ አገር ሰው የሆነው ቢልዳድና የናዕማ አገር ሰው የሆነው ጾፋር፥ እነዚህ ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች ነበሩ። እነርሱም በኢዮብ ላይ የደረሰውን ሥቃይ በሰሙ ጊዜ ሐዘናቸውን ሊገልጹለትና ሊያጽናኑት ከየአገራቸው ተጠራርተው በአንድነት ወደ ኢዮብ መጡ። 12ገና በሩቅ ሳሉ ኢዮብን አዩት፤ ሆኖም እርሱ መሆኑን በቀላሉ ለይተው ሊያውቁት አልቻሉም። በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ትቢያ ወደ ሰማይ እየበተኑና በራሳቸውም ላይ እየነሰነሱ በመጮኽ ማልቀስ ጀመሩ። 13የሥቃዩንም ብዛት ስላዩ ምንም ቃል ሳይናገሩ ከእርሱ ጋር ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊት በመሬት ላይ ተቀምጠው ሰነበቱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ