የዮሐንስ ወንጌል 3:22-36

የዮሐንስ ወንጌል 3:22-36 አማ05

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ፤ በዚያም እያጠመቀ ከእነርሱ ጋር ለጥቂት ጊዜ ቈየ። በዚያኑ ጊዜ ዮሐንስም ብዙ ውሃ ስለ ነበረበት በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም እየመጡ ይጠመቁ ነበር። በዚያን ጊዜ ዮሐንስ ገና አልታሰረም ነበር። በዚያን ጊዜ በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ መንጻት ሥርዓት ክርክር ተነሣ። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ዮሐንስ ቀርበው “መምህር ሆይ፥ ያ ከዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው፥ አንተ ስለ እርሱ የመሰከርክለት፥ እነሆ፥ እርሱም ያጠምቃል፤ ሰዎችም ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዳሉ” አሉት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ማንም ሰው እግዚአብሔር ካልሰጠው በቀር ምንም ነገር ሊኖረው አይችልም፤ ‘ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንጂ እኔ መሲሕ አይደለሁም’ ብዬ እንደ ነገርኳችሁ እናንተ ራሳችሁ ምስክሮቼ ናችሁ። ሙሽሪት ያለችው ሰው ሙሽራ ነው፤ የሙሽራው ሚዜ ግን ከሙሽራው አጠገብ ቆሞ ይሰማዋል፤ የእርሱንም ድምፅ በመስማት ይደሰታል፤ ስለዚህ የእኔም ደስታ ይህ ነው፤ እርሱም አሁን ፍጹም ሆኖአል። እርሱ ከፍ ከፍ ማለት ይገባዋል፤ እኔ ግን ዝቅ ዝቅ ማለት ይገባኛል።” ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነ ምድራዊ ነው፤ የምድርንም ነገር ይናገራል፤ ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። እርሱ ያየውንና የሰማውን ይመሰክራል፤ ነገር ግን የእርሱን ምስክርነት የሚቀበል የለም። የእርሱን ምስክርነት የሚቀበል ግን እግዚአብሔር እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጣል። እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጠው መጥኖ ስላልሆነ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል። አብ ልጁን ይወዳል፤ ሁሉንም ነገር በእጁ አስረክቦታል። በወልድ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በእርሱ ላይ ይኖርበታል እንጂ ሕይወትን አያገኝም።