ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ አገር ሄዱ፤ እዚያም ከእነርሱ ጋራ ጥቂት ተቀመጠ፤ አጠመቀም። በዚህ ጊዜ ዮሐንስም በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ብዙ ውሃ ስለ ነበረ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም ለመጠመቅ ይመጡ ነበር። ይህም የሆነው ዮሐንስ ወህኒ ከመግባቱ በፊት ነበር። በአንዳንድ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአንድ አይሁዳዊ መካከል ስለ መንጻት ሥርዐት ክርክር ተነሣ፤ ወደ ዮሐንስም መጥተው፣ “ረቢ፤ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋራ የነበረው፣ ስለ እርሱም የመሰከርህለት ሰው እነሆ፤ ያጠምቃል። ሰውም ሁሉ ወደ እርሱ እየሄደ ነው” አሉት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከላይ ካልተሰጠው በቀር ማንም አንዳች ሊቀበል አይችልም። ‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከርሱ በፊት ተልኬአለሁ’ እንዳልሁ እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። ሙሽራዪቱ የሙሽራው ናት፤ ድምፁን ለመስማት በአጠገቡ የሚቆመው ሚዜ ግን፣ የሙሽራውን ድምፅ ሲሰማ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ያ ደስታ የእኔ ነው፤ እርሱም አሁን ተፈጽሟል። እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ግን ላንስ ይገባል። “ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነው የምድር ነው፤ የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ያየውንና የሰማውን ይመሰክራል፤ ነገር ግን ምስክርነቱን ማንም አይቀበልም፤ ምስክርነቱንም የተቀበለ ሰው፣ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አረጋገጠ። እግዚአብሔር መንፈሱን ሳይሰፍር ስለሚሰጥ፣ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል። አብ ወልድን ይወድዳል፤ ሁሉንም ነገር በእጁ ሰጥቶታል። በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በላዩ ይሆናል እንጂ ሕይወትን አያይም።”
ዮሐንስ 3 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 3:22-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች