የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 3

3
ኒቆዲሞስ በስውር ወደ ኢየሱስ እንደ መጣ
1ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ የአይሁድ አለቃ ነበረ። 2ይህ ሰው በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ፦ “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በቀር እነዚህን አንተ የምታደርጋቸውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል ማንም የለም፤ ስለዚህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደ ሆንክ እናውቃለን” አለው።
3ኢየሱስም “እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ ሰው እንደገና ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው።
4ኒቆዲሞስም “ታዲያ፥ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ ወደ እናቱ ማሕፀን ገብቶ መወለድ ይችላልን?” ሲል ጠየቀ።
5ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። 6ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው። 7ስለዚህ ‘ዳግመኛ መወለድ ያስፈልጋችኋል’ ስላልኩህ አትደነቅ። 8ነፋስ ወደ ፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደሚመጣና ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።”
9ኒቆዲሞስም “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው።
10ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ይህን አታውቅምን? 11እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉትም። 12ምድራዊውን ነገር ስነግራችሁ የማታምኑ ከሆነ ሰማያዊውን ነገር ስነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? 13ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። #3፥13 ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም።፦ “በሰማይ ከሚኖረው ከሰው ልጅ በቀር” የሚሉ አንዳንድ የብራና ጽሑፎች አሉ።
14“ሙሴ በበረሓ እባብን ከፍ አድርጎ እንደ ሰቀለ እንዲሁም የሰው ልጅ ከፍ ብሎ ሊሰቀል ይገባዋል። #ዘኍ. 21፥9። 15ይህም የሚሆነው በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለምን ሕይወት እንዲያገኝ ነው።
16“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለ ወደደው አንድያ ልጁን ሰጠ። 17እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው፥ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለም።
18“በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ ቀድሞውኑ ተፈርዶበታል።
19“ፍርዱም ይህ ነው፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። 20ክፉ ነገር የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ ክፉ ሥራውም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። 21እውነት የሆነውን ነገር የሚያደርግ ግን ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ወደ ብርሃን የሚመጣውም ያደረገው ነገር በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት መሆኑ በግልጥ እንዲታይ ነው።”
መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ መመስከሩ
22ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ፤ በዚያም እያጠመቀ ከእነርሱ ጋር ለጥቂት ጊዜ ቈየ። 23በዚያኑ ጊዜ ዮሐንስም ብዙ ውሃ ስለ ነበረበት በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም እየመጡ ይጠመቁ ነበር። 24በዚያን ጊዜ ዮሐንስ ገና አልታሰረም ነበር። #ማቴ. 14፥3፤ ማር. 6፥17፤ ሉቃ. 3፥19-20።
25በዚያን ጊዜ በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ መንጻት ሥርዓት ክርክር ተነሣ። #3፥25 በአይሁድ፦ አንዳንድ የብራና ጽሑፎች “በጥቂት አይሁድ” ይላሉ። 26የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ዮሐንስ ቀርበው “መምህር ሆይ፥ ያ ከዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው፥ አንተ ስለ እርሱ የመሰከርክለት፥ እነሆ፥ እርሱም ያጠምቃል፤ ሰዎችም ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዳሉ” አሉት።
27ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ማንም ሰው እግዚአብሔር ካልሰጠው በቀር ምንም ነገር ሊኖረው አይችልም፤ 28‘ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንጂ እኔ መሲሕ አይደለሁም’ ብዬ እንደ ነገርኳችሁ እናንተ ራሳችሁ ምስክሮቼ ናችሁ። #ዮሐ. 1፥20። 29ሙሽሪት ያለችው ሰው ሙሽራ ነው፤ የሙሽራው ሚዜ ግን ከሙሽራው አጠገብ ቆሞ ይሰማዋል፤ የእርሱንም ድምፅ በመስማት ይደሰታል፤ ስለዚህ የእኔም ደስታ ይህ ነው፤ እርሱም አሁን ፍጹም ሆኖአል። 30እርሱ ከፍ ከፍ ማለት ይገባዋል፤ እኔ ግን ዝቅ ዝቅ ማለት ይገባኛል።”
31ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነ ምድራዊ ነው፤ የምድርንም ነገር ይናገራል፤ ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። 32እርሱ ያየውንና የሰማውን ይመሰክራል፤ ነገር ግን የእርሱን ምስክርነት የሚቀበል የለም። 33የእርሱን ምስክርነት የሚቀበል ግን እግዚአብሔር እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጣል። 34እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጠው መጥኖ ስላልሆነ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል።
35አብ ልጁን ይወዳል፤ ሁሉንም ነገር በእጁ አስረክቦታል። #ማቴ. 11፥27፤ ሉቃ. 10፥22። 36በወልድ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በእርሱ ላይ ይኖርበታል እንጂ ሕይወትን አያገኝም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ