ትንቢተ ኤርምያስ 43
43
ኤርምያስ ወደ ግብጽ መወሰዱ
1አምላካቸው እግዚአብሔር እንድነግራቸው ያዘዘኝን ሁሉ ለሕዝቡ ተናግሬ ፈጸምኩ፤ 2ከዚያ በኋላ የሆሻያ ልጅ ዐዛርያስ፥ የቃሬሐ ልጅ ዮሐናንና ትዕቢተኞች የሆኑ ሌሎችም ሰዎች ሁሉ እንዲህ አሉ፦ “ውሸትህን ነው፤ አምላካችን እግዚአብሔር እኛ ወደ ግብጽ ሄደን እዚያ እንዳንኖር ትነግረን ዘንድ አላከህም፤ 3ባቢሎናውያን በእኛ ላይ እንዲሠለጥኑብንና ቢፈልጉ እንዲገድሉን ወይም ወደ ባቢሎን ማርከው እንዲወስዱን ያነሣሣ የኔሪያ ልጅ ባሮክ ነው፤” 4በዚህም ዐይነት ዮሐናንም ሆነ የሠራዊት አለቆች ሁሉ፥ እንዲሁም ከሕዝቡ ወገን ማንም በይሁዳ ምድር ለመኖር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልፈጸሙም፤ 5ከዚህም በኋላ ዮሐናንና የሠራዊት አለቆች በይሁዳ የተረፉትን በሙሉ ወደ ግብጽ ወሰዱ፤ ይኸውም ከዚህ በፊት በአሕዛብ መካከል ተበታትነው ከቈዩ በኋላ እንደገና ወደ ይሁዳ አገር ተመልሰው የነበሩትን ሕዝብ ማለትም፥ 6ወንዶችንም ሴቶችንም፥ ሕፃናትንና የንጉሡን ሴቶች ልጆች ጭምር ወሰዱአቸው፤ የባቢሎን ጦር አዛዥ ናቡዛርዳን በገዳልያ ሥልጣን ሥር እንዲጠበቁ የተዋቸውን ሁሉ፥ እንዲሁም እኔንና ባሮክን ወሰዱ። 7የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጣስ ወደ ግብጽ ሄደው እስከ ጣፍናስ ከተማ ደረሱ። #2ነገ. 25፥26።
8በዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 9“ጥቂት ታላላቅ ድንጋዮች ፈልገህ ካገኘህ በኋላ ከእስራኤል ልጆች ጥቂቱ እያዩህ በከተማይቱ ቤተ መንግሥት መግቢያ ፊት ለፊት ባለው ከሲሚንቶ በተሠራው ወለል ሥር ቅበረው። 10ከዚያም የእስራኤል አምላክ እኔ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አገልጋዬ የሆነውን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ወደዚህ ስፍራ አምጥቼ አንተ በቀበርካቸው በእነዚያ ድንጋዮች ላይ ዙፋኑን ዘርግቶ የቤተ መንግሥት ድንኳኖቹን የሚተክልባቸው መሆኑን ንገራቸው። 11ናቡከደነፆር መጥቶ ግብጽን ድል ይነሣል፤ በበሽታ እንዲሞቱ የተወሰነባቸው በበሽታ ይሞታሉ፤ ተማርከው እንዲወሰዱ የተወሰኑ ይማረካሉ፤ በጦርነት እንዲሞቱ የተወሰኑ በጦርነት ይገደላሉ። 12በግብጽ የጣዖትን ቤተ መቅደሶች ያቃጥላል፤ ጣዖቶቹን ይማርካል፤ እረኛ ለምዱን እንደሚደርብ ግብጽን በግዛቱ ላይ ደርቦ ምንም ጒዳት ሳይደርስበት በድል አድራጊነት ይወጣል። 13በግብጽ ውስጥ በሄሊዮፖሊስ ከተማ የሚገኙትን ከድንጋይ የተሠሩ ሐውልቶችን ይደመስሳል፤ የግብጻውያንን ጣዖቶችንና ቤተ መቅደሶችን ያቃጥላል።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 43: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997