ትንቢተ ኤርምያስ 42

42
ኤርምያስ ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልይላቸው ሕዝቡ መጠየቃቸው
1የሠራዊት አለቆች፥ የቃሬሐ ልጅ ዮሐናንና የሆሻያ ልጅ ዐዛርያስ ሕዝቡም ሁሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ወደ እኔ መጥተው እንዲህ አሉኝ፦ 2“እባክህ የምንጠይቅህን ነገር አድርግልን! ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን! ከስደት ለተረፍነው ሁሉ ጸልይልን! ቀድሞ ብዙዎች ነበርን፤ አሁን ግን አንተ ራስህ እንደምታየን ጥቂቶች ብቻ ቀርተናል፤ 3ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር በየት አቅጣጫ መሄድ እንዳለብንና ምን ማድረግ እንደሚገባን ይገልጥልን ዘንድ ጸልይልን።”
4እኔም “መልካም ነው፤ ልክ እናንተ በጠየቃችሁት መሠረት ወደ እግዚአብሔር አምላካችሁ እጸልይላችኋለሁ፤ የሚገልጥልኝንም ሁሉ ከእናንተ ምንም ነገር ሳልሰውር እነግራችኋለሁ” ብዬ መለስኩላቸው።
5ከዚህም በኋላ እነርሱ እንዲህ አሉኝ “አምላክህ እግዚአብሔር በአንተ አማካይነት የሚሰጠንን ትእዛዝ ሁሉ በመፈጸም ለቃሉ ታዛዦች ሆነን ባንገኝ፥ እርሱ ራሱ በእኛ ላይ እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁንብን! 6መልካም ቢሆንም ባይሆንም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ቃል እንታዘዛለን፤ ወደ እርሱ የምንልክህም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብናከብር ሁሉ ነገር የሚሳካልን በመሆኑ ነው።”
ለኤርምያስ ጸሎት እግዚአብሔር የሰጠው መልስ
7ከዐሥር ቀን በኋላ እግዚአብሔር ተናገረኝ፤ 8ስለዚህም ዮሐናንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን የሠራዊት አለቆች ሕዝቡንም ሁሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ወደ እኔ እንዲመጡ ጠራኋቸው፤ 9እንዲህም አልኳቸው፦ “ጥያቄአችሁን ወደ እርሱ እንዳቀርብ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 10‘በዚህች ምድር የምትኖሩ ቢሆን እኔ እንደገና አንጻችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፤ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም፤ በእናንተ ላይ ያመጣሁት ጥፋት ታላቅ ሐዘን ሆኖብኛል፤ 11አሁን እንደምትፈሩት የባቢሎንን ንጉሥ ከእንግዲህ ወዲያ አትፍሩት፤ እኔ ከእናንተ ጋር ስለ ሆንኩ ከእርሱ ኀይል እታደጋችኋለሁ፤ 12እኔ እራራላችኋለሁ፤ እርሱም እንዲራራላችሁና ወደ አገራችሁ እንዲመልሳችሁ አደርጋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’
13“ነገር ግን እናንተ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ በዚህች ምድር አንቀመጥም ብትሉ፥ 14ደግሞም ‘እኛ የጦርነት ወሬና የእምቢልታ ድምፅ ወደማይሰማባት፥ ራብም ወደሌለባት ወደ ግብጽ ወርደን በዚያ እንኖራለን’ ብትሉ፥ 15እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ! እግዚአብሔር ስለ እናንተ የሚለውን ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ ግብጽ ወርዳችሁ በዚያ ለመኖር ብትወስኑ፥ 16ያ የምትፈሩት ጦርነት ይደርስባችኋል፤ የምትፈሩትም ራብ ተከትሎአችሁ ይሄዳል፤ በዚያም በግብጽ ትሞታላችሁ። 17ወደ ግብጽ ሄደው ለመኖር የወሰኑ ሁሉ፥ በጦርነት ወይም በራብ ወይም በወረርሽኝ ያልቃሉ፤ ከእነርሱ አንድ እንኳ አይተርፍም፤ በእነርሱ ላይ ላመጣው ካቀድኩት መቅሠፍትም የሚያመልጥ አይኖርም።’
18“የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ ግብጽ እንሄዳለን ብላችሁ ብትወስኑ ከዚህ በፊት በኢየሩሳሌም ሕዝብ ላይ የወረደው ቊጣዬና መዓቴ በእናንተም ላይ ይወርዳል፤ ለሕዝብ ሁሉ አስፈሪ መቀጣጫ ትሆናላችሁ፤ የሚያዩአችሁም ሕዝብ ሁሉ መዘባበቻ ያደርጓችኋል፤ ስማችሁም ለመሳለቂያ ይሆናል፤ ይህችንም ስፍራ ዳግመኛ አታዩአትም።’ ”
19-20“እናንተ ከስደት የተረፋችሁ የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ወደ እግዚአብሔር በላካችሁኝ ጊዜ እርሱ የሚያዘውን ሁሉ ንገረንና እንፈጽማለን ብላችሁ የማትፈጽሙትን ቃል በመግባታችሁ አደገኛ ስህተት ሠርታችኋል፤ አሁንም እግዚአብሔር ወደ ግብጽ አትሂዱ ብሎ ስለ ከለከለ እኔም ዛሬ ይህ ትእዛዝ እርግጠኛ መሆኑን በመግለጥ አስጠነቅቃችኋለሁ። 21እነሆ ዛሬ እኔም መልሱን ነገርኳችሁ፤ እናንተ ግን እግዚአብሔር አምላካችሁ እንድነግራችሁ በእኔ አማካይነት ለላከላችሁ ቃል ሁሉ ታዛዦች አልሆናችሁም። 22ስለዚህ አሁን ሄዳችሁ ልትኖሩ በምትፈልጉበት ቦታ በጦርነት፥ በራብና በወረርሽኝ እንደምትሞቱ እርግጠኞች ሁኑ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ