ትንቢተ ኤርምያስ 44
44
በግብጽ ለሚኖሩ እስራኤላውያን የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል
1በሰሜን ግብጽ ውስጥ ሚግዶል፥ ጣፍናስና ሜምፊስ ተብለው በሚጠሩት ከተሞችና በአገሪቱም ደቡባዊ ክፍል ተበታትነው ስለሚኖሩት እስራኤላውያን ሁሉ እግዚአብሔር ተናገረኝ፤ 2የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “በኢየሩሳሌምና በሌሎችም የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ያመጣሁትን ጥፋት እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፤ አሁንም እንኳ እንደ ፈራረሱ ናቸው፤ ማንም አይኖርባቸውም፤ 3ይህም የሆነበት ምክንያት በእነዚያ ከተሞች ይኖሩ የነበሩ ሕዝብ ክፉ ሥራ በመሥራት ስላስቈጡኝ ነው፤ እነርሱ ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት አቀረቡ፤ እነርሱም ሆኑ እናንተ ወይም የቀድሞ አባቶቻችሁ ያላመለኩአቸውን አማልክት አመለኩ፤ 4እኔ የምጠላቸውን እነዚህን አጸያፊ ነገሮች እንዳታደርጉ ያስጠነቅቋችሁ ዘንድ አገልጋዮቼን ነቢያትን ወደ እናንተ ደጋግሜ ልኬ ነበር። 5እናንተ ግን እነርሱን ማዳመጥም ሆነ ለሚናገሩት ቃል ዋጋ ልትሰጡት አልፈለጋችሁም፤ ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት የማቅረብ ክፉ ልምዳችሁን መተው አልፈለጋችሁም፤ 6ስለዚህም በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ ቊጣዬንና መዓቴን በማፍሰስ በእሳት እንዲጋዩ አደረግሁ፤ እነርሱም ዛሬ እንደሚታዩት ሁሉ ፍርስራሾችና ባድማ ሆነዋል።
7“አሁንም እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እስቲ ልጠይቃችሁ፦ እናንተስ ራሳችሁ ለምን ይህን ሁሉ ክፉ ነገር ታደርጋላችሁ? ከይሁዳ ሕዝብ መካከል አንድ እንኳ ለዘር እንዳይተርፍ በወንዶችና በሴቶች፥ በልጆችና በሕፃናት ላይ ጥፋት እንዲመጣ ለምን ትፈልጋላችሁ? 8መጥታችሁ በምትኖሩባት በዚህችስ በግብጽ ምድር ለጣዖቶች በመስገድና ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት በማቅረብ ስለምን ታስቈጡኛላችሁ? ወይስ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ እንዲዘባበቱባችሁና ስማችሁንም መራገሚያ ያደርጉት ዘንድ ራሳችሁን በራሳችሁ ማጥፋት ትፈልጋላችሁን? 9በቀድሞ አባቶቻችሁ፥ በይሁዳ ነገሥታትና በሚስቶቻቸው፥ በእናንተ በራሳችሁና በሚስቶቻችሁ አማካይነት በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ የተፈጸመውን ክፉ ሥራ ሁሉ ረስታችሁታልን? 10ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ራሳችሁን ዝቅ በማድረግ ትሑታን ሆናችሁ አልተገኛችሁም፤ ለእኔ ክብር አልሰጣችሁኝም፤ ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለእናንተ በሰጠሁትም ሕግና ደንብ ጸንታችሁ መኖር አልፈለጋችሁም።
11“ስለዚህም የእስራኤል አምላክ እኔ የሠራዊት ጌታ በእናንተ ላይ በቊጣ ተነሣሥቼ ይሁዳን በሙሉ እደመስሳለሁ፤ 12በይሁዳ ከስደት ከተረፉት መካከል ወደ ግብጽ ወርደው በዚያ ለመኖር የወሰኑትን ሁሉ እንዲጠፉ አደርጋለሁ፤ ከትልቅ እስከ ትንሽ በጦርነት ወይም በረሀብ በግብጽ አገር ይሞታሉ። እነርሱም ለሕዝቦች አስደንጋጭ ይሆናሉ፤ ሕዝብም ሁሉ ይዘባበትባቸዋል፤ ስማቸውንም መራገሚያ ያደርጉታል። 13ኢየሩሳሌምን በጦርነት፥ በራብና በቸነፈር እንደቀጣሁ፥ በግብጽ የሚኖሩትንም እቀጣለሁ፤ 14በይሁዳ ከስደት ተርፈው ወደ ግብጽ ወርደው ከሚኖሩት መካከል አንድ እንኳ የሚያመልጥ ወይም የሚተርፍ አይኖርም፤ እንደገና ይኖሩባት ዘንድ ወደሚናፍቋት ወደ ይሁዳ የሚመለስ ማንም አይኖርም፤ ከጥቂት ስደተኞች በቀር ተመልሶ የሚመጣ አይኖርም።”
15ሚስቶቻቸው ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚያቀርቡ መሆናቸውን የሚያውቁ ወንዶች ሁሉ፥ በግብጽ ደቡባዊ ክፍል የሚኖሩት እስራኤላውያንና በዚያ ቆመው የነበሩት ሴቶች ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው በመቅረብ እንዲህ አሉኝ፦ 16“አንተ በእግዚአብሔር ስም የተናገርከውን ሁሉ መስማት አንፈልግም፤ 17እኛ እንፈጽማለን ብለን ያሰብነውን ነገር ሁሉ እናደርጋለን፤ የሰማይ ንግሥት ተብላ ለምትጠራው አምላካችን ዕጣን እናጥናለን፤ እኛና የቀድሞ አባቶቻችን፥ ንጉሦቻችንና መሪዎቻችን በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ስናደርግ በነበረው ዐይነት አሁንም የወይን ጠጅ መባ እናቀርብላታለን። ይህን ሁሉ በምናደርግበት በዚያን ጊዜ ብዙ ሲሳይ ነበረን፤ ባለጸጎችም ስለ ነበርን ምንም ችግር አልነበረብንም። 18ነገር ግን ለሰማይ ንግሥት የሚቃጠል መሥዋዕትና ለእርስዋም የወይን ጠጅ መባ ማቅረብን ካቋረጥንበት ጊዜ ጀምሮ ምንም ያተረፍነው ነገር የለም፤ ሕዝባችንም በጦርነትና በረሀብ አልቆአል።”
19ሴቶችም ጨምረው ሲናገሩ፥ “በሰማይ ንግሥት እንጎቻ በምንጋግርበት ጊዜ፥ ለእርስዋ መሥዋዕትና የወይን ጠጅ መባ በምናቀርብበት ጊዜ፥ ከባሎቻችን ተለይተን ያደረግነው ነገር አልነበረም።”
20በዚህ ዐይነት የመለሱልኝን ወንዶች፥ ሴቶችና ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አልኳቸው፦ 21“እናንተና የቀድሞ አባቶቻችሁ፥ ንጉሦቻችሁና መሪዎቻችሁ፥ በምድሪቱም የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ፥ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ዕጣን ታጥኑ እንደ ነበረ፥ እግዚአብሔር አያስበውም ወይም ረስቶታል ብላችሁ ታስባላችሁን? 22እነሆ በአሁኑ ጊዜ ምድራችሁ ፍርስራሽ ሆናለች፤ የሚኖርባትም የለም፤ ምድሪቱ አጸያፊ ሆናለች፤ ሕዝብም ሁሉ እንደ ተረገመች ይቈጥሩአታል፤ እግዚአብሔር የዐመፅና የክፋት ሥራችሁን ሁሉ አይታገሥም። 23ይህም ሁሉ መቅሠፍት የደረሰባችሁ ለባዕዳን አማልክት መሥዋዕት በማቅረባችሁ፥ እግዚአብሔርን በማሳዘናችሁ፥ ለሕጉ፥ ለድንጋጌውና ለሥርዓቱም ባለመታዘዛችሁ ነው።”
24-25ከይሁዳ ተሰደው በግብጽ ስለሚኖሩት ሕዝብ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ የነገረኝን ሁሉ ለሕዝቡ ሁሉ በተለይም ለሴቶቹ እንዲህ በማለት ነገርኳቸው፦ “እናንተና ሚስቶቻችሁ ለሰማይ ንግሥት ስእለት ለመስጠት ቃል ገብታችኋል፤ ይኸውም እናንተ ለእርስዋ ዕጣን ልታጥኑላት፥ የወይን ጠጅም መባ ልታፈሱላት የገባችሁትን ቃል ኪዳን ፈጽማችኋል፤ እንግዲያውስ ቀጥሉ፤ የገባችሁትን ቃል ጠብቁ፤ መሐላችሁንም ፈጽሙ፤ 26ነገር ግን በግብጽ ስለምትኖሩ እስራኤላውያን ሁሉ እኔ እግዚአብሔር በኀያሉ ስሜ በመማል የወሰንኩትን ስሙ፤ ከእናንተ ማንም ሰው ‘ሕያው ልዑል እግዚአብሔርን’ ብሎ በስሜ እንዲምል አልፈቅድም። 27ደግ ነገር ሳይሆን ክፉ ነገር እንዲደርስባችሁ አደርጋለሁ፤ ከእናንተ አንድ እንኳ ሳይተርፍ ሁላችሁም በጦርነትና በረሀብ ትሞታላችሁ፤ 28ነገር ግን ከእናንተ ጥቂቶች ብቻ ከሞት ተርፈው ከግብጽ ወደ ይሁዳ ይመለሳሉ፤ በዚያን ጊዜ ወደ ግብጽ የወረዱ ስደተኞች የእኔ ወይስ የእናንተ የማንኛችን ቃል እውነት እንደ ሆነ ያረጋግጣሉ፤ 29በዚህ ቦታ በምቀጣችሁ ጊዜ ‘በእናንተ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ’ ብዬ የተናገርኩት ቃል እውነት እንደሚሆን እኔ እግዚአብሔር አረጋግጥላችኋለሁ፤ 30እኔ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ቀድሞ ጠላቱ ለነበረና ይገድለው ዘንድ ለሚፈልገው ለባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አሳልፌ እንደ ሰጠሁት ሁሉ፥ ሖፍራ ተብሎ የሚጠራውን የግብጽ ንጉሥ ሊገድሉት ለሚፈልጉ ጠላቶቹ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።” #2ነገ. 25፥1-7።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 44: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997