የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 30

30
እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠው ተስፋ
1ወደ ኤርምያስ የመጣው የእስራኤል አምላክ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 2“የነገርኩህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፍ። 3ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን እንደገና የምመልስበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ ለቀድሞ አባቶቻቸው ወደ ሰጠኋቸው ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም እንደገና የራሳቸው ያደርጓታል። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
4እግዚአብሔር ለእስራኤልና ለይሁዳ ሕዝብ የሚለው ይህ ነው፤
5“የሰላም ሳይሆን የመሸበርና
የመርበድበድ ድምፅ ይሰማል፤
6እስቲ ቆም ብላችሁ አስቡ!
ወንድ አምጦ ልጅን መውለድ ይችላልን?
ታዲያ ወንድ ሁሉ እንደ ወላድ ሴት
በእጆቹ ወገቡን ይዞ የማየው ስለምንድን ነው?
የእያንዳንዱስ ሰው ፊት ስለምን ገረጣ?
7ያ ቀን ምንኛ አስጨናቂ ይሆናል!
እርሱን የመሰለ ቀን የለም፤
ለያዕቆብ ልጆች ለእስራኤላውያን የመከራ ዘመን ይሆናል፤
ሆኖም እነርሱ ከዚያ ሁሉ ጭንቀት ይድናሉ።”
8የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ያ ቀን በደረሰ ጊዜ በሕዝቤ ጫንቃ ላይ የተጫነውን የአገዛዝ ቀንበር እሰብራለሁ፤ ሰንሰለታቸውንም አስወግዳለሁ፤ ከዚያን በኋላ ለባዕዳን ሕዝብ ባሪያዎች አይሆኑም፤ 9በዚህ ፈንታ ለእኔ ለአምላካቸው ይሰግዱልኛል፤ እኔ በዙፋን ላይ ለማስቀምጥላቸው የዳዊት ዘር ለሆነውም ንጉሣቸው ይገዛሉ።
10የአገልጋዬ የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ፥
አትፍሩ ተስፋም አትቊረጡ፤
ከሩቅ አገር በደኅና እመልሳችኋለሁ፤ ልጆቻችሁንም
ተማርከው ከተወሰዱበት አገር እመልሳቸዋለሁ፤
እስራኤላውያን እንደገና ሰላም አግኝተው
ያለ ስጋት ይኖራሉ።
11እኔ ራሴ ከእናንተ ጋር በመሆን አድናችኋለሁ፤
እናንተን የበተንኩባቸውን አሕዛብ ሁሉ እደመስሳለሁ፤
እናንተን ግን አላጠፋም፤
ሆኖም ያለ ቅጣት አልተዋችሁም፤
የምቀጣችሁ ግን እንደ ጥፋታችሁ ነው፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” #ኤር. 46፥27-28።
12እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ይላል፦
“ቊስላችሁ የማይፈወስ፥
ጒዳታችሁም ከባድ ነው።
13ለእናንተ የሚከራከርላችሁ የለም፤
ለቊስላችሁም መድኃኒት አይገኝም፤
እናንተም አትድኑም።
14ወዳጆቻችሁ ሁሉ ረስተዋችኋል፤
እነርሱ እናንተን አይፈልጉአችሁም፤
ኃጢአታችሁ የበዛ፥
ክፋታችሁም እጅግ ከፍ ያለ ስለ ሆነ፥
እንደ ጠላት መታኋችሁ፤
ያለ ርኅራኄም ቀጣኋችሁ።
15ኃጢአታችሁ የበዛ
ክፋታችሁም እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ
ፈውስ ስለማይገኝላችሁ፥
ስለ ቊስላችሁ ሕመም አታጒረምርሙ፤
እኔ እንዲህ አድርጌ እቀጣችኋለሁ።
16ነገር ግን እናንተን ግጠው የበሉአችሁ ሁሉ
እነርሱም በፈንታቸው ተግጠው ይበላሉ፤
ጠላቶቻችሁ ሁሉ ተማርከው ይወሰዳሉ፤
ሲዘርፉአችሁ የነበሩት ሁሉ ይዘረፋሉ።
የቀሙአችሁ ሁሉ እነርሱም በተራቸው እንዲቀሙ አደርጋለሁ።
17ጠላቶቻችሁ ‘ጽዮን እንደ ተጣለች መቅረትዋ ነው፤
የሚጠነቀቅላትም የለም’ ቢሉም፥
እኔ ጤንነታችሁን እንደገና እመልስላችኋለሁ፤
ቊስላችሁንም እፈውሳለሁ፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
18እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የእስራኤልን ልጆች ቤት መልሼ እሠራለሁ፤
ለያንዳንዱም ቤተሰብ ምሕረቴን እልካለሁ፤
የኢየሩሳሌም ከተማ እንደገና ትሠራለች፤
ቤተ መንግሥቱም በድሮ ቦታ ተመልሶ ይታነጻል።
19በዚያም የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ፥
የምስጋና መዝሙር ይዘምራሉ፤
በደስታም እልል ይላሉ፤
አበዛቸዋለሁ እንጂ ቊጥራቸው አይቀንስም፤
ክብር እንዲኖራቸው አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ አይናቁም።
20ልጆቻቸው እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው ተፈርተው ይኖራሉ፤
ይህም ማኅበራዊ ኑሮአቸው በፊቴ የጸና ይሆናል፤
ሲጨቊኑአቸው የነበሩትንም ሁሉ እቀጣለሁ።
21የራሳቸው ወገን ከመካከላቸው ተነሥቶ
መሪአቸው ይሆናል፤
እኔ ራሴ ስለማመጣው እርሱ ወደ እኔ ይቀርባል፤
አለበለዚያማ ማን ደፍሮ ሊቀርብ ይችላል?
22እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤
እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
23እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለው የእግዚአብሔር ቊጣ እንደ ኀይለኛ ነፋስ እየተገለባበጠ በክፉዎች ራስ ላይ ይወርዳል። 24ኀይለኛው የእግዚአብሔር ቊጣ ሊያደርገው ያቀደውንም ነገር ሳይፈጽም አይመለስም፤ ጊዜው ሲደርስ ሕዝቡ ራሳቸው ይህን ሁሉ በግልጥ ይረዱታል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ