ትንቢተ ኤርምያስ 29

29
ኤርምያስ በባቢሎን ለሚኖሩ አይሁድ የላከው ደብዳቤ
1ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ለወሰዳቸው ካህናትና ነቢያት ለሕዝብ አለቆችና ለሌሎችም ስደተኞች ሁሉ ከኢየሩሳሌም የጻፍኩት ደብዳቤ ይዘት እንዲህ የሚል ነው፤ 2ደብዳቤውንም የጻፍኩት ንጉሡ ኢኮንያን፥ እቴጌይቱ እናቱና የቅርብ አገልጋዮቹ፥ የይሁዳና የኢየሩሳሌም መሪዎች፥ የእጅ ጥበብ ሠራተኞችና ሙያተኞች ሁሉ ተማርከው ከተወሰዱ በኋላ ነው፤ #2ነገ. 24፥12-16፤ 2ዜ.መ. 36፥10። 3ደብዳቤውንም የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላካቸው በሻፋን ልጅ በኤልዓሳና በሕልቂያ ልጅ በገማርያ እጅ ላክሁት፤ የደብዳቤውም ፍሬ ነገር እንዲህ የሚል ነው፦ 4“ከኢየሩሳሌም አስማርኮ ወደ ባቢሎን ላስወሰዳቸው ሕዝብ ሁሉ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ 5‘ቤት ሠርታችሁ ኑሩ፤ አትክልት ትከሉ፤ ፍሬውንም ብሉ፤ 6እየተጋባችሁ ልጆችን ውለዱ፤ ልጆቻችሁም በተራቸው እየተጋቡ ልጆችን ይውለዱ፤ ቊጥራችሁ ይብዛ እንጂ አይቀንስ፤ 7ተማርካችሁ ሄዳችሁ እንድትኖሩባቸው ላደረግኋቸው ከተሞችም ዕድገት መልካም ነገርን ተመኙ፤ ስለ እነርሱም መልካም ኑሮ ወደ እኔ ጸልዩ፤ እነርሱ መልካም ኑሮ ቢኖሩ እናንተም መልካም ኑሮን ትኖራላችሁ። 8እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ በመካከላችሁ በሚኖሩ ነቢያት ወይም የወደፊቱን ሁኔታ እናውቃለን በሚሉ ሰዎች ሁሉ እንዳትታለሉ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ ለሕልሞቻቸውም ትኲረት አትስጡአቸው። 9እነርሱ በእኔ ስም የሚነግሩአችሁ ትንቢት ሁሉ ሐሰት ነው፤ እኔ ከቶ አላክኋቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ”
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በባቢሎን የምትኖሩበት ሰባው ዓመት ከተፈጸመ በኋላ እንደገና እናንተን በምሕረት እጐበኛለሁ፤ ወደ አገራችሁ እንድመልሳችሁ የገባሁትን ቃል ኪዳን እፈጽማለሁ፤ #2ዜ.መ. 36፥21፤ ኤር. 25፥11፤ ዳን. 9፥2። 11ስለ እናንተ ያለኝን ዕቅድ የማውቅ እኔ ነኝ፤ ይህም ዕቅድ ክፋትን ሳይሆን ሰላምን በማስገኘት እናንተ በተስፋ የምትጠብቁት መልካም ነገር የሚፈጸምበት ነው፤ 12ከዚያን በኋላ እናንተ ትጠሩኛላችሁ፤ ወደ እኔም ቀርባችሁ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ፤ 13ትፈልጉኛላችሁ፤ የምትፈልጉኝም በሙሉ ልባችሁ ከሆነ ታገኙኛላችሁ፤ #ዘዳ. 4፥29። 14በእርግጥ እላችኋለሁ ታገኙኛላችሁ፤ እኔም ወደ ምድራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ እናንተን ከበተንኩበት ከየትኛውም አገርና ከየትኛውም ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ እኔ እናንተን ነቅዬ እንድትሰደዱ ከማድረጌ በፊት ወደ ነበራችሁበት ምድር መልሼ አመጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
15“እግዚአብሔር በባቢሎን ነቢያትን አስነሥቶልናል” ብላችሁ ተናግራችኋል። 16የዳዊትን ዙፋን ወርሶ ገዢ ስለ ሆነው ንጉሥና እንደ እናንተ ተማርከው ስላልተወሰዱት በዚህች ከተማ ስለሚገኙት ዘመዶቻችሁ እግዚአብሔር የሚለውን ቃል ስሙ። 17የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እኔ በእነርሱ ላይ ጦርነትን፥ ራብንና ቸነፈርን ላመጣባቸው ነው፤ ከመበላሸቱ የተነሣ ሊበሉት እንደማይቻል የበለስ ዛፍ ፍሬ አደርጋቸዋለሁ፤ 18በጦርነት፥ በራብና በቸነፈር አባርራቸዋለሁ፤ የዓለም ሕዝብ ሁሉ በእነርሱ ላይ ስለሚያዩት ነገር ይደነግጣሉ፤ እንዲበተኑ በማደርግበት ስፍራ ሁሉ በእነርሱ ላይ የማደርሰውን ነገር የሚያዩ ሕዝቦች ሁሉ በመደንገጥ ይሸበራሉ። ሕዝብም ሁሉ መሳቂያና መሳለቂያ ያደርጋቸዋል። 19ይህም ሁሉ የሚደርስባቸው በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት በመደጋገም የላክሁላቸውን ቃሌን ካለመስማትና ካለመታዘዝ የተነሣ ነው። 20ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን እንድትሰደዱ ያደረግኋችሁ እናንተም ሁላችሁ እኔ እግዚአብሔር የምለውን ቃል ስሙ።”
21“በእግዚአብሔር ስም የሐሰት ትንቢት ቃል ስለሚነግሩአችሁም ስለ ቆላያ ልጅ አክዓብና ስለ ማዕሤያ ልጅ ሴዴቅያስ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፦ ‘እነርሱን ዐይናችሁ እያየ በፊታችሁ በሞት ለሚቀጣቸው ለባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ 22ከኢየሩሳሌም ተማርከው ወደ ባቢሎን የተሰደዱ ሕዝብ ሁሉ በአንድ ሰው ላይ የእርግማን ቃል መናገር ሲፈልጉ፥ ‘እግዚአብሔር የባቢሎን ንጉሥ በሕይወት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ ያድርግህ’ ይላሉ፤ 23ዕድል ፈንታቸውም ይህ የሚሆንበት ምክንያት አሠቃቂ ኃጢአት በመሥራታቸው ነው፤ ይኸውም ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ጋር አመንዝረዋል፤ እኔም ያላዘዝኳቸውን የሐሰት ቃል በስሜ ተናግረዋል፤ ይህም እኔ ያልፈቀድኩት ነገር ነው፤ ያደረጉትን ሁሉ ስለማውቅባቸው በእነርሱ ላይ እመሰክርባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ”
ሸማዕያ የላከው ደብዳቤ
24-25የኔሔላም ተወላጅ ለሆነው ለሸማዕያ፥ እንዲህ በለው፤ ይህ የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክ ቃል ነው፤ ለኢየሩሳሌም ሰዎች ለካህኑ ለማዕሲያ ልጅ ለሰፎንያስና ለሌሎቹም ካህናት በራስህ ስም መልእክቶችን ልከሃል፤ በመልእክትህም ለሰፎንያስ እንዲህ ብለኸዋል፦ 26“እግዚአብሔር በካህኑ በዮዳሄ ቦታ ካህን አድርጎ ሾሞሃል፤ እነሆ የቤተ መቅደሱም የበላይ አለቃ አንተ ነህ፤ ስለዚህም ነቢይ ነኝ እያለ በማስመሰል የሚናገረውን አንዳንድ ዕብድ በአንገት ሰንሰለትና በእግር ግንድ እየጠፈሩ ማሰር የአንተ ተግባር መሆን አለበት፤ 27ታዲያ ነቢይ ነኝ እያለ ለሕዝቡ የሚናገረውን የዐናቶት ተወላጅ የሆነውን ኤርምያስን ለምን አልገሠጽከውም? 28እርሱ እንዳይናገር መከልከል አለበት፤ ምክንያቱም ወደ ባቢሎን ተማርከው የተወሰዱት ሕዝብ ገና ብዙ ዘመን መኖር እንዳለባቸው በመቊጠር ‘ቤት ሠርታችሁ ተደላድላችሁ ኑሩ፤ አትክልት ትከሉ፤ ፍሬውንም ብሉ’ እያለ ለሕዝቡ ተናግሮአል።”
29ሶፎንያስ ደብዳቤውን ለእኔ ለኤርምያስ አነበበልኝ፤ 30ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 31“እነሆ ተሰደው በባቢሎን ወደሚኖሩት ሁሉ ስለ ሽማዕያ የተነገረውን ይህን የትንቢት ቃል እንዲህ ብለህ ላክ፥ ‘ሽማዕያ እኔ ሳልከው የትንቢት ቃል በመናገር በውሸት እንድታምኑ አድርጓችኋል፤ 32ስለዚህም እኔ እግዚአብሔር እርሱንና ዘሮቹን ሁሉ እቀጣለሁ፤ ከእንግዲህ ይህ ሰው በእናንተ መካከል የሚተርፍ ዘር አይኖረውም፤ እርሱ ራሱም ለሕዝቤ የማደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ለማየት የመኖር ተስፋ የለውም፤ ምክንያቱም እርሱ እናንተን በእኔ ላይ እንድታምፁ አድርጓችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ ”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ