ትንቢተ ኤርምያስ 23:9-40

ትንቢተ ኤርምያስ 23:9-40 አማ05

ስለ ነቢያት በማስብበት ጊዜ ልቤ በሐዘን ይሰበራል፤ አጥንቶቼም ይንቀጠቀጣሉ፤ ከእግዚአብሔር ከቅዱስ ቃሉ የተነሣ፥ በወይን ጠጅ እንደ ተሸነፈ ሰካራም ሆኜአለሁ፤ ምድሪቱ እግዚአብሔርን በተዉ አመንዝሮች ተሞልታለች፤ ነቢያቱ ኀይላቸውን ያለ አግባቡ ይጠቀማሉ፤ የክፋትንም መንገድ ይከተላሉ፤ ከእግዚአብሔር ርግማን የተነሣ፥ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ መስኮችም ደርቀዋል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የነቢያቱና የካህናቱ መንፈሳዊ ሕይወት ተበላሽቶአል፤ ሌላው ቀርቶ በቤተ መቅደስ ውስጥ እንኳ ክፉ ነገርን ያደርጋሉ፤ ስለዚህም መንገዳቸው የሚያዳልጥ መሬት ይሆናል፤ በጨለማም ሲራመዱ መንገዳቸውን ስተው ይወድቃሉ፤ በሚቀጡበትም ቀን ክፉ ነገርን አመጣባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። የሰማርያ ነቢያት የሠሩትን አጸያፊ ነገር አይቼአለሁ፤ እነርሱ በበዓል ስም እየተነበዩ ሕዝቤን እስራኤልን ያስታሉ። ነገር ግን በኢየሩሳሌም የሚገኙ ነቢያትም ከዚህ የባሰ ክፋት ሲያደርጉ አይቼአለሁ፤ እነርሱ ያመነዝራሉ፤ ሐሰትም ይናገራሉ፤ ሰዎችን ለክፉ ሥራ ያነሣሣሉ፤ ከዚህም የተነሣ ሕዝቡ ከክፉ ሥራቸው አይመለሱም። ስለዚህ እነርሱ በእኔ ዘንድ እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ሕዝብ የከፉ ናቸው። “እንግዲህ እኔ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኢየሩሳሌም ነቢያት የምለው ይህ ነው፦ ‘በምድሪቱ ሁሉ ላይ የክሕደትን መንፈስ ስላሠራጩ፥ መራራ ቅጠል እንዲበሉና መርዝ እንዲጠጡ አደርጋቸዋለሁ።’ ” የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “ነቢያቱ የሚሉትን አትስሙ፤ እነርሱ በሐሰተኛ ተስፋ ይሞሉአችኋል፤ የሚነግሩአችሁም በሐሳባቸው ያለሙትን እንጂ እኔ የምነግራቸውን ቃል አይደለም፤ የእኔን ቃል መስማት የማይፈልጉትን ሕዝቦች ‘አይዞአችሁ፥ ሰላም ይሆንላችኋል’ ይሉአቸዋል፤ እለኸኛ የሆነውንም ሁሉ ‘አይዞህ ምንም ችግር አይደርስብህም’ ይሉታል።” ከእነርሱ መካከል በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ቆሞ ቃሉን ያዳመጠና ለቃሉም ትኲረት ሰጥቶ ታዛዥ የሆነ ማነው? የእግዚአብሔር ቊጣ በክፉዎች ራስ ላይ እንደሚተም ማዕበልና እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ሲወርድ ተመልከት። እግዚአብሔር ያቀደውን ተግባራዊ አድርጎ እስኪፈጽም ድረስ ቊጣው ከቶ አይገታም፤ ወደ ፊት ሕዝቡ ይህን ሁሉ በግልጥ ይረዱታል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በራሳቸው ፈቃድ ፈጥነው ሄዱ እንጂ እኔ እነዚህን ነቢያት አላክኋቸውም፤ እኔ ምንም የትንቢት ቃል አልሰጠኋቸውም፤ እነርሱ ግን በስሜ ትንቢት ይናገራሉ፤ በእኔ ጉባኤ ፊት ቆመው ቢሆንማ ኖሮ ቃሌን ለሕዝቡ ባወጁ ነበር፤ ጠማማ መንገዳቸውንና ክፉ አኗኗራቸውንም ትተው ወደ እኔ እንዲመለሱ ማድረግ በቻሉ ነበር።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የቅርብ አምላክ ብቻ ነኝን? የእሩቅስ አምላክ አይደለሁምን? እኔ ሰማይንና ምድርን የሞላሁ አይደለሁምን? ሰው በስውር ቦታ ቢሸሸግ እኔ አላየውምን? በስሜ ሐሰት የሚናገሩት ነቢያት የሚሉትን ሰማሁ፤ ‘ሕልም አልሜአለሁ፥ ሕልም ዐልሜአለሁ’ እያሉ ይጮኻሉ። እነዚያ ነቢያት ራሳቸው በአእምሮአቸው ውስጥ እንዲከሠት ባደረጉት የሐሰት ትንቢት ሕዝቤን የሚያስቱት እስከ መቼ ነው? አባቶቻቸው በዓልን በማምለክ ስሜን እንደ ረሱ እነርሱም ሕልሞቻቸውን እርስ በርሳቸው በመነጋገር ሕዝቤ የእኔን ስም የሚረሳ ይመስላቸዋል። ሕልም ያለመ ነቢይ ቢኖር ሕልሙን ብቻ ይናገር፤ ቃሌን የሰማ ነቢይ ግን ያንኑ ቃል በታማኝነት ይናገር፤ ገለባ ከስንዴ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ቃሌ እንደ እሳት፥ አለቱንም ሰባብሮ እንደሚያደቅ መዶሻ ነው። አንዱ ከሌላው ቃልን በመስረቅ ‘ይህ የእግዚአብሔር ቃል ነው’ እያሉ የሚናገሩትን ነቢያት እጠላለሁ። እንዲሁም ከራሳቸው አመንጭተው እየተናገሩ ‘ይህ የእግዚአብሔር ቃል ነው’ የሚሉትን ነቢያት እቃወማለሁ። እነሆ እኔ እግዚአብሔር የምለውን አድምጡ! በሐሰት የተሞላ ሕልማቸውን የሚናገሩ ነቢያትን እጠላለሁ፤ ይህን ሕልም እየተናገሩ ሐሰት በተሞላ ትምክሕታቸው ሕዝቤን ከእውነተኛ መንገድ ያወጣሉ፤ እኔ አላክኋቸውም፤ ወይም ሂዱልኝ አላልኳቸውም፤ ለሕዝቡም የሚሰጡት ጥቅም የለም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፥ “ኤርምያስ ሆይ! ነቢይ ወይም ካህን ወይም ከሕዝቤ አንዱ፥ ‘የእግዚአብሔር ሸክም ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፥ ‘የእግዚአብሔር ሸክም እናንተ ናችሁ፤ ስለ ሆነም ከፊቱ ያስወግዳችኋል’ ብለህ ንገራቸው። ነቢይ ወይም ካህን ወይም ከሕዝቡ አንዱ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ብሎ ከተናገረ እርሱንም ቤተሰቡንም እቀጣለሁ። በዚህ ፈንታ እያንዳንዱ ‘እግዚአብሔር የሰጠው መልስ ምንድን ነው? እግዚአብሔር የተናገረውስ ምንድን ነው?’ በማለት ወዳጆቹንና ዘመዶቹን መጠየቅ አለበት። የእግዚአብሔር ሸክም ብላችሁ ከቶ አትናገሩ፤ የእግዚአብሔር ቃል እንዴት ሸክም ሊሆን ይችላል? እናንተ ግን የሠራዊት ጌታ የሕያው እግዚአብሔርን ቃል ታጣምማላችሁ። አንተም ኤርምያስ ሆይ፥ ነቢዩን ‘እግዚአብሔር ምን መልስ ሰጠህ? ምንስ ተናገረህ’ ብለህ ጠይቀው። ከእነርሱ መካከል ግን ትእዛዜን አፍርሰው፥ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ብለው የሚናገሩ ከሆነ፥ ‘የእግዚአብሔር ሸክም አትበሉ’ ብዬ ብልክባቸውም እንኳ፥ እነርሱ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ስላሉ እኔ ራሴ እናንተን፥ እነርሱን፥ ለእነርሱና ለቀድሞ አባቶቻቸው የሰጠሁትን ከተማ እንደ ሸክም ተሸክሜ ከፊቴ እንደማስወግድ ንገራቸው። በእነርሱም ላይ ከቶ የማይረሳ ዘለዓለማዊ ኀፍረትና ውርደት አመጣባቸዋለሁ።”