የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 23

23
ስለ ወደፊቱ ተስፋ
1“የእግዚአብሔር መንጋ የሆነውን ሕዝብ ለሚበትኑና ለሚያጠፉ መሪዎች ወዮላቸው!” ይላል እግዚአብሔር፤ 2የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሕዝቡ ጠባቂዎች መሆን ስለሚገባቸው መሪዎች እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤን እንደሚገባ አልጠበቃችሁም፤ ይልቁንም አሳዳችሁ በተናችሁ፤ ስለዚህ ስለ ፈጸማችሁት ክፋት ሁሉ እቀጣችኋለሁ። 3የቀሩትን ሕዝቤን ከበተንኳቸው አገር ሁሉ ሰብስቤ ወደ ትውልድ አገራቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ብዙ ልጆች ስለሚወልዱ ቊጥራቸው እየጨመረ ይሄዳል። 4የሚጠብቁአቸውን መሪዎች እሾምላቸዋለሁ፤ ሕዝቤ ከእንግዲህ ወዲህ ያለ ፍርሀትና ያለ ድንጋጤ ይኖራሉ፤ እኔም ዳግመኛ አልቀጣቸውም፤ ወይም ከእነርሱ አንድም አይጐድልም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከዳዊት ዘር መካከል ጻድቅ የሆነውን ለንጉሥነት የምመርጥበት ጊዜ ይመጣል፤ ያም ንጉሥ በጥበብ ያስተዳድራል፤ በምድሪቱም ሁሉ ላይ ትክክልና ቅን የሆነውን ነገር ያደርጋል። 6እርሱ በሚነግሥበት ጊዜ የይሁዳ ሕዝብ ደኅንነት ያገኛል፤ የእስራኤልም ሕዝብ በሰላም ይኖራል፤ እርሱም ‘እግዚአብሔር ጽድቃችን’ ተብሎ ይጠራል። #ኤር. 33፥14-16።
7“ሰዎች ‘የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው የማይምሉበት ጊዜ ይመጣል። 8በዚህ ፈንታ፥ የእስራኤልን ሕዝብ ከሰሜን ምድርና ተበታትነው ከነበሩባቸው ሌሎች አገሮች ሰብስቤ ባመጣኋቸው በእኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም ይምላሉ፤ ከዚያም በኋላ በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ።”
ኤርምያስ ስለ ሐሰተኞች ነቢያት የተናገረው የትንቢት ቃል
9ስለ ነቢያት በማስብበት ጊዜ ልቤ በሐዘን ይሰበራል፤
አጥንቶቼም ይንቀጠቀጣሉ፤
ከእግዚአብሔር ከቅዱስ ቃሉ የተነሣ፥
በወይን ጠጅ እንደ ተሸነፈ ሰካራም ሆኜአለሁ፤
10ምድሪቱ እግዚአብሔርን በተዉ አመንዝሮች ተሞልታለች፤
ነቢያቱ ኀይላቸውን ያለ አግባቡ ይጠቀማሉ፤ የክፋትንም መንገድ ይከተላሉ፤
ከእግዚአብሔር ርግማን የተነሣ፥
ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ መስኮችም ደርቀዋል።
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“የነቢያቱና የካህናቱ መንፈሳዊ ሕይወት ተበላሽቶአል፤
ሌላው ቀርቶ በቤተ መቅደስ ውስጥ እንኳ ክፉ ነገርን ያደርጋሉ፤
12ስለዚህም መንገዳቸው የሚያዳልጥ መሬት ይሆናል፤
በጨለማም ሲራመዱ መንገዳቸውን ስተው ይወድቃሉ፤
በሚቀጡበትም ቀን ክፉ ነገርን አመጣባቸዋለሁ፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
13የሰማርያ ነቢያት የሠሩትን አጸያፊ ነገር አይቼአለሁ፤
እነርሱ በበዓል ስም እየተነበዩ ሕዝቤን እስራኤልን ያስታሉ።
14ነገር ግን በኢየሩሳሌም የሚገኙ ነቢያትም
ከዚህ የባሰ ክፋት ሲያደርጉ አይቼአለሁ፤
እነርሱ ያመነዝራሉ፤ ሐሰትም ይናገራሉ፤
ሰዎችን ለክፉ ሥራ ያነሣሣሉ፤
ከዚህም የተነሣ ሕዝቡ ከክፉ ሥራቸው አይመለሱም።
ስለዚህ እነርሱ በእኔ ዘንድ
እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ሕዝብ የከፉ ናቸው። #ዘፍ. 18፥20፤ ሕዝ. 16፥49።
15“እንግዲህ እኔ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኢየሩሳሌም ነቢያት የምለው ይህ ነው፦
‘በምድሪቱ ሁሉ ላይ የክሕደትን መንፈስ ስላሠራጩ፥
መራራ ቅጠል እንዲበሉና መርዝ እንዲጠጡ አደርጋቸዋለሁ።’ ”
16የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “ነቢያቱ የሚሉትን አትስሙ፤ እነርሱ በሐሰተኛ ተስፋ ይሞሉአችኋል፤ የሚነግሩአችሁም በሐሳባቸው ያለሙትን እንጂ እኔ የምነግራቸውን ቃል አይደለም፤ 17የእኔን ቃል መስማት የማይፈልጉትን ሕዝቦች ‘አይዞአችሁ፥ ሰላም ይሆንላችኋል’ ይሉአቸዋል፤ እለኸኛ የሆነውንም ሁሉ ‘አይዞህ ምንም ችግር አይደርስብህም’ ይሉታል።”
18ከእነርሱ መካከል በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ቆሞ ቃሉን ያዳመጠና ለቃሉም ትኲረት ሰጥቶ ታዛዥ የሆነ ማነው? 19የእግዚአብሔር ቊጣ በክፉዎች ራስ ላይ እንደሚተም ማዕበልና እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ሲወርድ ተመልከት። 20እግዚአብሔር ያቀደውን ተግባራዊ አድርጎ እስኪፈጽም ድረስ ቊጣው ከቶ አይገታም፤ ወደ ፊት ሕዝቡ ይህን ሁሉ በግልጥ ይረዱታል።
21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በራሳቸው ፈቃድ ፈጥነው ሄዱ እንጂ እኔ እነዚህን ነቢያት አላክኋቸውም፤ እኔ ምንም የትንቢት ቃል አልሰጠኋቸውም፤ እነርሱ ግን በስሜ ትንቢት ይናገራሉ፤ 22በእኔ ጉባኤ ፊት ቆመው ቢሆንማ ኖሮ ቃሌን ለሕዝቡ ባወጁ ነበር፤ ጠማማ መንገዳቸውንና ክፉ አኗኗራቸውንም ትተው ወደ እኔ እንዲመለሱ ማድረግ በቻሉ ነበር።”
23እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የቅርብ አምላክ ብቻ ነኝን? የእሩቅስ አምላክ አይደለሁምን? 24እኔ ሰማይንና ምድርን የሞላሁ አይደለሁምን? ሰው በስውር ቦታ ቢሸሸግ እኔ አላየውምን? 25በስሜ ሐሰት የሚናገሩት ነቢያት የሚሉትን ሰማሁ፤ ‘ሕልም አልሜአለሁ፥ ሕልም ዐልሜአለሁ’ እያሉ ይጮኻሉ። 26እነዚያ ነቢያት ራሳቸው በአእምሮአቸው ውስጥ እንዲከሠት ባደረጉት የሐሰት ትንቢት ሕዝቤን የሚያስቱት እስከ መቼ ነው? 27አባቶቻቸው በዓልን በማምለክ ስሜን እንደ ረሱ እነርሱም ሕልሞቻቸውን እርስ በርሳቸው በመነጋገር ሕዝቤ የእኔን ስም የሚረሳ ይመስላቸዋል። 28ሕልም ያለመ ነቢይ ቢኖር ሕልሙን ብቻ ይናገር፤ ቃሌን የሰማ ነቢይ ግን ያንኑ ቃል በታማኝነት ይናገር፤ ገለባ ከስንዴ ጋር ምን ግንኙነት አለው? 29ቃሌ እንደ እሳት፥ አለቱንም ሰባብሮ እንደሚያደቅ መዶሻ ነው። 30አንዱ ከሌላው ቃልን በመስረቅ ‘ይህ የእግዚአብሔር ቃል ነው’ እያሉ የሚናገሩትን ነቢያት እጠላለሁ። 31እንዲሁም ከራሳቸው አመንጭተው እየተናገሩ ‘ይህ የእግዚአብሔር ቃል ነው’ የሚሉትን ነቢያት እቃወማለሁ። 32እነሆ እኔ እግዚአብሔር የምለውን አድምጡ! በሐሰት የተሞላ ሕልማቸውን የሚናገሩ ነቢያትን እጠላለሁ፤ ይህን ሕልም እየተናገሩ ሐሰት በተሞላ ትምክሕታቸው ሕዝቤን ከእውነተኛ መንገድ ያወጣሉ፤ እኔ አላክኋቸውም፤ ወይም ሂዱልኝ አላልኳቸውም፤ ለሕዝቡም የሚሰጡት ጥቅም የለም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
የሐሰተኞች ነቢያት ትንቢት
33እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፥ “ኤርምያስ ሆይ! ነቢይ ወይም ካህን ወይም ከሕዝቤ አንዱ፥ ‘የእግዚአብሔር ሸክም ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፥ ‘የእግዚአብሔር ሸክም እናንተ ናችሁ፤ ስለ ሆነም ከፊቱ ያስወግዳችኋል’ ብለህ ንገራቸው። 34ነቢይ ወይም ካህን ወይም ከሕዝቡ አንዱ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ብሎ ከተናገረ እርሱንም ቤተሰቡንም እቀጣለሁ። 35በዚህ ፈንታ እያንዳንዱ ‘እግዚአብሔር የሰጠው መልስ ምንድን ነው? እግዚአብሔር የተናገረውስ ምንድን ነው?’ በማለት ወዳጆቹንና ዘመዶቹን መጠየቅ አለበት። 36የእግዚአብሔር ሸክም ብላችሁ ከቶ አትናገሩ፤ የእግዚአብሔር ቃል እንዴት ሸክም ሊሆን ይችላል? እናንተ ግን የሠራዊት ጌታ የሕያው እግዚአብሔርን ቃል ታጣምማላችሁ። 37አንተም ኤርምያስ ሆይ፥ ነቢዩን ‘እግዚአብሔር ምን መልስ ሰጠህ? ምንስ ተናገረህ’ ብለህ ጠይቀው። 38ከእነርሱ መካከል ግን ትእዛዜን አፍርሰው፥ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ብለው የሚናገሩ ከሆነ፥ ‘የእግዚአብሔር ሸክም አትበሉ’ ብዬ ብልክባቸውም እንኳ፥ እነርሱ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ስላሉ 39እኔ ራሴ እናንተን፥ እነርሱን፥ ለእነርሱና ለቀድሞ አባቶቻቸው የሰጠሁትን ከተማ እንደ ሸክም ተሸክሜ ከፊቴ እንደማስወግድ ንገራቸው። 40በእነርሱም ላይ ከቶ የማይረሳ ዘለዓለማዊ ኀፍረትና ውርደት አመጣባቸዋለሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ