ኤርምያስ 23:9-40

ኤርምያስ 23:9-40 NASV

ስለ ነቢያት፣ ልቤ በውስጤ ተሰብሯል፤ ዐጥንቶቼም ተብረክርከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ፣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ፣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው፣ እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ። ምድሪቱ በአመንዝሮች ተሞልታለች፤ ከርግማን የተነሣ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ በምድረ በዳ ያሉት መሰማሪያዎች ደርቀዋል። ነቢያቱም ጠማማ መንገድ ተከትለዋል፤ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል። “ነቢዩም፣ ካህኑም በጽድቅ መንገድ የማይሄዱ ናቸው፤ በቤተ መቅደሴ እንኳ ሳይቀር ክፋታቸውን አይቻለሁ።” ይላል እግዚአብሔር። “ስለዚህ መንገዳቸው ድጥ ይሆናል፤ ወደ ጨለማ ይጣላሉ፤ ተፍገምግመውም ይወድቃሉ፤ በሚቀጡበትም ዓመት፣ መዓት አመጣባቸዋለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር። “በሰማርያ ባሉ ነቢያት ላይ፣ ደስ የማያሰኝ ነገር አይቻለሁ፤ በበኣል ስም ትንቢት ተናገሩ፤ ሕዝቤን እስራኤልን አሳቱ። በኢየሩሳሌም ባሉ ነቢያትም ላይ፣ የሚዘገንን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ፤ በመዋሸትም ይኖራሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ፣ የክፉዎችን እጅ ያበረታሉ፤ በእኔ ዘንድ ሁሉም እንደ ሰዶም፣ ነዋሪዎቿም እንደ ገሞራ ናቸው።” ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ነቢያት እንዲህ ይላል፤ “ከኢየሩሳሌም ነቢያት፣ በምድሪቱ ሁሉ ርኩሰት ተሠራጭቷልና፤ መራራ ምግብ አበላቸዋለሁ፤ የተመረዘም ውሃ አጠጣቸዋለሁ።” የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነዚህ ነቢያት የሚተነብዩላችሁን አትስሙ፤ በባዶ ተስፋ ይሞሏችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ሳይሆን፣ ከገዛ ልባቸው የሆነውን ራእይ ይናገራሉ። እኔን ለሚንቁኝ፣ ‘እግዚአብሔር ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል’ ይላሉ፤ የልባቸውን እልኸኝነት ለሚከተሉም ሁሉ፣ ‘ክፉ ነገር አይነካችሁም’ ይሏቸዋል። ቃሉን ለማየትና ለመስማት፣ እነማን የእግዚአብሔር ምክር ባለበት ቆመዋል? ቃሉን ያደመጠ፣ የሰማስ ማን ነው? እነሆ፤ የእግዚአብሔር ዐውሎ ነፋስ፣ በቍጣ ይነሣል፤ ብርቱም ማዕበል፣ የክፉዎችን ራስ ይመታል። እግዚአብሔር የልቡን ሐሳብ፣ ሙሉ በሙሉ ሳይፈጽም፣ ቍጣው እንዲሁ አይመለስም፤ በኋለኛው ዘመን፣ ይህን በግልጽ ትረዳላችሁ። እኔ እነዚህን ነቢያት አልላክኋቸውም፤ እነርሱ ግን ለራሳቸው መልእክታቸውን ይዘው ሮጡ፣ ሳልናገራቸውም፣ ትንቢት ተናገሩ። ምክሬ ባለበት ቢቆሙ ኖሮ፣ ቃሌን ለሕዝቤ ባሰሙ ነበር፤ ከክፉ መንገዳቸው፣ ከክፉ ሥራቸውም በመለሷቸው ነበር። “እኔ የቅርብ አምላክ ብቻ ነኝን?” ይላል እግዚአብሔር፤ “የሩቅስ አምላክ አይደለሁምን? እኔ እንዳላየው፣ በስውር ቦታ ሊሸሸግ የሚችል አለን?” ይላል እግዚአብሔር። “ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን” ይላል እግዚአብሔር። “ ‘ሕልም ዐለምሁ ሕልም ዐለምሁ’ እያሉ በስሜ የሐሰት ትንቢት የሚናገሩትን የነቢያትን ቃል ሰምቻለሁ፤ ይህ ነገር፣ የገዛ ልባቸውን ሽንገላ በሚተነብዩ በሐሰተኞች ነቢያት ልብ ውስጥ የሚቈየው እስከ መቼ ነው? አባቶቻቸው በኣልን በማምለክ ስሜን እንደ ረሱ፣ እነርሱ በሚነጋገሩት ሕልም፣ ሕዝቤ ስሜን እንዲረሳ ያደረጉ ይመስላቸዋል። ሕልመኛ ነቢይ ሕልሙን ያውራ፤ ቃሌ ያለው ግን በታማኝነት ይናገር፤ ገለባና እህል ምን አንድ አድርጓቸው!” ይላል እግዚአብሔር። “ቃሌ እንደ እሳት፣ ድንጋይንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለምን?” ይላል እግዚአብሔር። “ስለዚህ ቃሌን እርስ በእርስ በመሰራረቅ ከእኔ እንደ ተቀበሉ አድርገው የሚናገሩትን ነቢያት እቃወማለሁ” ይላል እግዚአብሔር። “አፈጮሌነታቸውን በመጠቀም፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ የሚሉትን ነቢያት እቃወማለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “እነሆ፤ ሐሰተኛ ሕልም ተመርኵዘው ትንቢት የሚናገሩትን ነቢያት እቃወማለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “እኔ ሳልልካቸው ወይም ሳልሾማቸው ደፍረው ውሸት ይናገራሉ፤ ሕዝቤንም ያስታሉ፤ ለዚህም ሕዝብ አንዳች አይረቡትም” ይላል እግዚአብሔር። “ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፣ ‘የእግዚአብሔር ሸክም ምንድን ነው?’ ብለው ቢጠይቁ፣ ‘ሸክሙ እናንተ ናችሁ፤ እወረውራችኋለሁ’ ይላል እግዚአብሔር ብለህ መልስላቸው። ነቢይ ወይም ካህን ወይም ማንኛውም ሰው፣ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ እያለ ቢናገር፣ ያን ሰውና ቤቱን እቀጣለሁ። እያንዳንዱ ለባልንጀራው ወይም ለዘመዱ፣ ‘እግዚአብሔር ምን መልስ ሰጠ?’ ወይም፣ ‘እግዚአብሔር ምን ተናገረ?’ ማለት ይገባዋል። ከእንግዲህ ግን፣ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ብላችሁ መናገር አይገባችሁም፤ ምክንያቱም ለሰው ሁሉ የገዛ ራሱ ቃል ሸክሙ ስለሚሆን፣ የአምላካችንን የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን፣ የሕያው አምላክን ቃል ታጣምማላችሁ። ስለዚህ ለነቢዩ፣ ‘እግዚአብሔር ምን መልስ ሰጠህ?’ ወይም፣ ‘እግዚአብሔር ምን ተናገረህ?’ ትለዋለህ፤ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ብትሉ እንኳ፣ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ፣ “የእግዚአብሔር ሸክም” አትበሉ’ ብዬ ብነግራችሁም፣ እናንተ፣ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ብላችኋል፤ ስለዚህ እናንተን፣ እንዲሁም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ የሰጠኋትን ከተማ ጭምር ፈጽሜ እተዋችኋለሁ፤ ከፊቴ እጥላችኋለሁ፤ ለዘላለም የማይረሳ ዕፍረት፣ የዘላለምም ውርደት አመጣባችኋለሁ።”