መጽሐፈ መሳፍንት 15:13-20

መጽሐፈ መሳፍንት 15:13-20 አማ05

እነርሱም “መልካም ነው፤ አንተን በገመድ አስረን ለእነርሱ አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ እኛስ አንገድልህም” ሲሉ መለሱለት። ከዚህም በኋላ በሁለት አዳዲስ ገመዶች አሰሩትና ከዋሻው አውጥተው ወሰዱት። ሶምሶንም ወደ ሌሒ በመጣ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እየደነፉ መጡበት፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አበረታው፤ ክንዱ የታሰሩበት ገመዶች እሳት እንደ ነካቸው የሐር ፈትል ከእጁ ላይ ቀልጠው ወደቁ። ከዚህ በኋላ በቅርብ ጊዜ የሞተ የአንድ አህያ መንጋጋ አገኘ፤ ጐንበስ ብሎ አንሥቶም አንድ ሺህ ሰው ገደለበት። ሶምሶንም፥ “በአህያ መንጋጋ አንድ ሺህ ሰው ገደልኩ፤ በዚህም የአህያ መንጋጋ ሬሳውን በሬሳ ላይ ከመርሁ” አለ። ከዚያም በኋላ ይዞት የነበረውን መንጋጋ ወረወረው፤ ይህም የተፈጸመበት ያ ስፍራ “ራማት ሌሒ” ተብሎ ተጠራ። ከዚህ በኋላ ሶምሶን በጣም ተጠማ፤ ወደ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ጮኸ፤ “ይህን ትልቅ ድል ለአገልጋይህ ሰጥተኸኛል፤ ታዲያ፥ እኔ አሁን በውሃ ጥም ልሙትን? ባልተገረዙ ሰዎች እጅም ልውደቅን?” እግዚአብሔር በሌሂ ያለው ጐድጓዳ ቦታ ከፈተለት፤ ከእርሱም ውሃ ወጣ፤ በጠጣም ጊዜ መንፈሱ ተመልሶለት ተጠናከረ፤ ስለዚህም ያ ቦታ “ዐይን ሃቆሬ” የተባለ። እርሱም እስከ ዛሬ ድረስ በሌሂ ይገኛል። ፍልስጥኤማውያን በሀገሩ ላይ ገዢዎች በነበሩበት ዘመን ሶምሶን እስራኤልን ለኻያ ዓመት ሙሉ መራ።