የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 24

24
የእግዚአብሔር ቊጣ በምድር ላይ
1እነሆ እግዚአብሔር ምድሪቱን አፈራርሶ ባድማ ያደርጋታል፤ የዚያችንም ምድር ገጽታ ለዋውጦ ሕዝቦችዋን ይበትናል፤ 2የሰው ሁሉ ዕድል አንድ ዐይነት ይሆናል፤ ካህናትና ሕዝቡ፥ አገልጋዮችና አሳዳሪዎቻቸው፥ እመቤቲቱና አገልጋይቱ፥ ገዢዎችና ሻጮች፥ አበዳሪዎችና ተበዳሪዎች፥ ዕዳ ከፋይና ዕዳ አስከፋይ በአንድነት ይጠፋሉ። 3ምድሪቱ ተበዝብዛ ባዶዋን ትቀራለች፤ ይህ ሁሉ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ስለ ሆነ ይፈጸማል።
4ምድሪቱ እጅግ ደርቃ ልምላሜዋ ሁሉ ይጠወልጋል፤ የምድርም ታላላቅ ሰዎች ይደክማሉ። 5ሰዎች ሕጎችን በመጣስ፥ ደንብን በመተላለፍና ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በማፍረስ ምድርን አርክሰዋል። 6ስለዚህም ርግማን ምድርን ያጠፋል፤ ሕዝቦችዋም በበደሉት በደል ተጠያቂዎች ይሆናሉ፤ ስለዚህ የምድር ነዋሪዎች ይደመሰሳሉ፤ የሚተርፉትም ጥቂቶች ናቸው። 7የወይን ተክሎች ደርቀዋል፤ የወይን ጠጅም ተወዶአል፤ በዚህ ምክንያት ከዚህ በፊት ይደሰት የነበረ ሁሉ አሁን ሐዘንተኛ ሆኖአል፤ 8የሚያስደስት የመሰንቆ፥ ሙዚቃና የአታሞ ድምፅ መሰማቱ ቀርቶአል፤ የበዓል አከባበር ሁሉ ቆሞአል። 9የወይን ጠጅ እየጠጡ በመዝፈን መደሰት አይኖርም፤ የሚያሰክር መጠጥም ለጠጪው መራራ ይሆናል። 10የፈረሰችው ከተማ ባድማ ትሆናለች፤ ማንም ሰው እንዳይገባበት ቤቱ ሁሉ ተዘግቶአል። 11ዳግመኛ የወይን ጠጅ ስለማይገኝ ሰዎች በየአደባባዩ ይጮኻሉ፤ ደስታ ለዘለዓለም ጠፍቶአል፤ ሐሴትም በምድር ላይ አይገኝም፤ 12ከተማይቱ የፍርስራሽ ክምር ሆናለች፤ በሮችዋም ተሰባብረው ወድቀዋል። 13በዓለም መንግሥታት ሁሉ ላይ የሚደርሰው ሁኔታ ይህ ነው፤ የወይራ ፍሬ ከዛፍ ሁሉ ላይ ተለቅሞ፥ የወይንም ዘለላ ከተሰበሰበ በኋላ እንደሚታይ የመከር መጨረሻ ይሆናል።
14ከጥፋት የተረፉት በደስታ እልል ይላሉ፤ በስተ ምዕራብ ያሉትም ሁሉ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ይናገራሉ። 15ስለዚህ በምሥራቅ ያሉት ለእግዚአብሔር ክብር ይሰጣሉ፤ በደሴቶች ያሉ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ስም ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። 16“ለጻድቁ ለእርሱ ክብር ይሁን!” የሚል መዝሙር ከዓለም ዳርቻ ይሰማል። እኔ ግን እጅግ በመክሳት ስለ መነመንኩ ወዮልኝ! ከዳተኞች በከዳተኝነታቸው ጸንተዋል፤ ከዳተኛነታቸውም እየባሰ ሄዶአል። 17በምድር ላይ የምትኖሩ ሁሉ! አድምጡኝ! ሽብር፥ ጒድጓድና ወጥመድ ይጠብቃችኋል። 18ከአሸባሪ ድምፅ የሚሸሽ በተቈፈረ ጒድጓድ ውስጥ ይወድቃል፤ ከጒድጓድ ዘሎ ለማምለጥ የሚሞክርም በወጥመድ ይያዛል፤ ከሰማይ ብርቱ ዝናብ ይዘንባል፤ የምድር መሠረቶችም ይናወጣሉ። 19ምድር ተናወጠች፤ ተሰነጣጥቃም ተከፋፈለች። 20ምድር እንደ ሰከረ ሰው ትንገዳገዳለች፤ በዐውሎ ነፋስ እንደ ተገፋ ጎጆም ትናወጣለች፤ እርስዋም የኃጢአትዋ ሸክም ስለሚጫናት ትወድቃለች፤ መነሣትም አትችልም።
21እግዚአብሔር በዚያን ዘመን የሰማይ ኀይላትንና የምድር ገዢዎችን የሚቀጣበት ጊዜ ይመጣል። 22እግዚአብሔር ነገሥታትን በአንድነት ሰብስቦ በምድር ውስጥ ባለ እስር ቤት ውስጥ እንዳሉ እስረኞች እንዲኖሩ ያደርጋል፤ ከብዙ ቀኖችም በኋላ ይቀጣቸዋል። 23የሠራዊት እምላክ ስለሚነግሥ ጨረቃ ትጨልማለች፥ ፀሐይም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ እርሱ በኢየሩሳሌም፥ በጽዮን ተራራ ላይ ሆኖ ያስተዳድራል፤ የሕዝቡ መሪዎች ሁሉ ክብሩን ያያሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ