የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 25

25
የምስጋና መዝሙር
1አምላክ ሆይ! አንተ አምላኬ ነህ፤
ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤
ስምህንም አመሰግናለሁ፤
አንተ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን አድርገሃል፤
ከጥንት ጀምሮ ያቀድከውን ሁሉ፥
ፍጹምነት ባለው አስተማማኝ ሁኔታ አከናውነሃል።
2ከተሞች ፈርሰው ባድማ እንዲሆኑ አድርገሃል፤
ምሽጎቻቸውንም አፈራርሰሃል፤
ጠላቶቻችን የሠሩአቸው ቤተ መንግሥቶች እንዳልነበሩ ሆነዋል፤
እስከ ዘለዓለምም እንደገና አይሠሩም።
3የታላላቅ መንግሥታት ሕዝቦች ያከብሩሃል፤
በጨካኞች መንግሥታት ከተሞች የሚኖሩ ሁሉ ይፈሩሃል።
4ለድኾች፥ ለመጻተኞችና ለችግረኞች
በችግራቸው ጊዜ መጠጊያ ሆነህላቸዋል፤
ከዐውሎ ነፋስ የሚድኑበት ተገንና
ከፀሐይ ቃጠሎ የሚጠለሉበት ጥላ ሆነህላቸዋል፤
የጨካኞች ምት የክረምት ወጀብ ግድግዳን እንደሚገፋ ያለ ነው።
5እነርሱ በደረቅ ቦታ ላይ እንዳለ ሙቀት ሕዝብን ይጐዳሉ፤
አምላክ ሆይ! አንተ ግን የባዕዳንን ድንፋታ ዝም አሰኘህ፤
የደመና ጥላ ቃጠሎን እንደሚያበርድ የጋጠወጦችን ዘፈን ጸጥ አደረግህ።
እግዚአብሔር የሚያዘጋጀው ታላቅ ግብዣ
6የሠራዊት አምላክ በዚህች በጽዮን ተራራ ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ ታላቅ ግብዣ ያዘጋጃል፤ በግብዣውም ላይ ምርጥ የወይን ጠጅና፥ የተሟላ ምግብ ይዘጋጃል። 7በዚህ ተራራ ላይ ሕዝቦችን ሁሉ ጋርዶ የነበረውን የሐዘን መጋረጃ ያስወግዳል። 8ልዑል እግዚአብሔር የሞትን ኀይል ለዘለዓለም ያጠፋል! ከሰዎችም ሁሉ ዐይን እንባን ያብሳል፤ ወገኖቹ በዓለም ሁሉ ላይ የተቀበሉትን ኀፍረት ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ራሱ ይህን ተናግሮአል። #1ቆሮ. 15፥54፤ ራዕ. 7፥17፤ 21፥4።
9ይህም በሚፈጸምበት ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ “እነሆ፥ እርሱ አምላካችን ነው፤ በእርሱ ስለ ታመንን አድኖናል፤ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ እኛም በእርሱ ታምነናል፤ እርሱ ስለ ታደገን በደስታ ተሞልተን ሐሴት እናደርጋለን!” ይላሉ።
እግዚአብሔር ሞአብን እንደሚቀጣ
10የእግዚአብሔር ኀይል የጽዮንን ተራራ ይጠብቃል። የሞአብ ሕዝብ ጭድ ከጭቃ ጋር በጒድጓድ ውስጥ እንደሚረገጥ ይረገጣሉ። 11እንደ ዋነተኛ እጆቻቸውን ይዘረጋሉ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በትዕቢታቸው ስለሚያዋርዳቸው እጆቻቸው ይዝለፈለፋሉ። 12የሞአብን ምሽጎች ከታላላቅ ግንቦቻቸው ጋር ያፈራርሳል፤ ተሰባብረውም ከትቢያ ጋር ይቀላቀላሉ። #ኢሳ. 15፥1—16፥14፤ ኤር. 48፥1-47፤ ሕዝ. 25፥8-11፤ አሞጽ 2፥1-3፤ ዘካ. 2፥8-11።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ