ትንቢተ ኢሳይያስ 23
23
ስለ ጢሮስ የተነገረ ትንቢት
1ስለ ጢሮስ ከተማ የተነገረ የትንቢት ቃል ይህ ነው፤ ጢሮስና ቤትዋ ወይም ወደብዋ የፈራረሱ ስለ ሆነ እናንተ የተርሴስ መርከቦች እሪ በሉ፤ ከቆጵሮስ ስትመለሱ የሚጠብቃችሁ ወሬ ይኸው ነው። 2መርከበኞች ያበለጸጉአችሁ እናንተ የደሴቲቱ ሕዝብና የሲዶን ነጋዴዎች በሐዘን ጸጥ በሉ! 3በግብጽ የሚመረተው እህል በትልቁ ባሕር በኩል መጥቶ ለጢሮስ ትልቅ ገቢ ይሆናል፤ ስለዚህ ጢሮስ የዓለም ገበያ ሆናለች። 4የሲዶና ከተማ ሆይ! አንቺ በባሕር አጠገብ የተገነባሽ ጠንካራ ምሽግ ነሽ፤ ነገር ግን አንቺ ባል አግብታ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወልዳ እንዳላሳደገች ሴት የተዋረድሽ ትሆኚአለሽ።
5ጢሮስ መደምሰስዋን በሰሙ ጊዜ ግብጻውያን በድንጋጤ ይታወካሉ።
6እናንተ በባሕር ጠረፍ የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ! በዋይታ እያለቀሳችሁ ወደ ተርሴስ ተሻገሩ። 7ሕዝቦችዋ ወደ ሩቅ አገር ሄደው ለመስፈር የቻሉት ለዘመናት ተደስታ ትኖር የነበረችው ከተማ እንዲህ ሆና ቀረችን? 8ዘውድን ታቀዳጅ በነበረችው ከተማ፥ ልዑላን የሆኑና በዓለም የተከበሩ ነጋዴዎች በነበርዋት በጢሮስ ላይ ይህን ሁሉ ያቀደ ማነው? 9ይህንማ ያቀደው የሠራዊት አምላክ ነው፤ እርሱም ይህን ያቀደው ባደረጉት ነገር መታበያቸውን እንዲተዉ ለማድረግና የተከበሩትንም ሰዎች ለማዋረድ ብሎ ነው።
10የተርሴስ ሕዝብ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲያ ወደብ ስለሌላችሁ ልክ በአባይ ወንዝ ዳር እንደሚደረገው ምድራችሁን እረሱ። 11መንግሥታትን በማናወጥ የእግዚአብሔር ኀይል እስከ ባሕር ማዶ ደርሶአል፤ በከነዓንም ምድርም ያሉ ምሽጎች እንዲፈርሱ አዞአል። 12“አንቺ የሲዶን ከተማ ሆይ! የደስታሽ ዘመን አክትሞአል፤ ሕዝብሽ ተጨቊነዋል፤ ወደ ቆጵሮስ ሸሽተው ቢያመልጡ እንኳ እዚያ በሰላም አይኖሩም” ብሎአል።
13እነሆ የባቢሎናውያንን ምድር ተመልከቱ፤ ሕዝቡ ዋጋቢስ ሆኖ ቀርቶአል፤ አሦራውያን ምድሪቱን የአራዊት መፈንጫ አድርገዋታል፤ ምሽጎችዋንም ሰባብረው፥ ምድሪቱን የፍርስራሽ ክምር በማድረግ የራሳቸውን ምሽግ አቁመውባታል።
14እናንተ በባሕር ላይ የምትመላለሱ የተርሴስ መርከበኞች! የምትኰሩባት ወደብ ስለ ተደመሰሰች በዋይታ አልቅሱ!
15ጢሮስ ሰባ ዓመት ያኽል ተረስታ የምትኖርበት ጊዜ ይመጣል፤ ይህም የአንድ ንጉሥ ዕድሜ ነው፤ እነዚያ ዓመቶች ካለፉ በኋላ ጢሮስ እንደ ዘማዊት ሴት እንዲህ ተብሎ ቅኔ የሚነገርባት ትሆናለች፦
16አንቺ የተረሳሽ ዘማዊት
በገናሽን እየደረደርሽ በከተማ ውስጥ ዙሪ!
እንዲያስታውሱሽ ጣዕመ ዜማ አሰሚ፤
ብዙ መዝሙሮችንም ዘምሪ!
17ከሰባ ዓመት በኋላ እግዚአብሔር ጢሮስን ይጐበኛታል፤ ወደ ቀድሞ የንግድ ሥራዋ እንድትመለስ ያደርጋታል፤ በምድር ላይ ከሚገኙ መንግሥታት ሁሉ ጋር ታመነዝራለች። 18በንግድ የምታገኘውም ገንዘብ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል፤ ለራስዋ ተቀማጭ ሳታደርግ የእግዚአብሔር አገልጋዮች በሚያስፈልጋቸው ምግብና በጥሩ ልብስ ያውሉታል። #ሕዝ. 26፥1—28፥19፤ ኢዩ. 3፥4-8፤ አሞጽ 1፥9-10፤ ዘካ. 9፥1-4፤ ማቴ. 11፥21-22፤ ሉቃ. 10፥13-14።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 23: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997