የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሐጌ 1:3-15

ትንቢተ ሐጌ 1:3-15 አማ05

ስለዚህም እግዚአብሔር በነቢዩ በሐጌ አማካይነት ለሕዝቡ የተናገረው ቃል የሚከተለው ነው፤ “ሕዝቤ ሆይ! የእኔ ቤት ፈርሶ ሳለ፥ እናንተ ተውበው በተሠሩ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? ያላችሁበትን ሁኔታ አስቡ። እነሆ ብዙ ዘርታችሁ ጥቂት ሰበሰባችሁ፤ ትበላላችሁ፤ ነገር ግን አትጠግቡም፤ ትጠጣላችሁ፤ ነገር ግን አትረኩም፤ ደራርባችሁ ትለብሳላችሁ፤ ነገር ግን አይሞቃችሁም፤ ሠርታችሁ የምታገኙት ደመወዝ ስለማይበረክትላችሁ፥ በቀዳዳ ኪስ ውስጥ የማኖር ያኽል ይሆናል። ያላችሁበትን ሁኔታ አስቡ። በሉ አሁን ወደ ኰረብቶች ውጡ፤ እንጨትም ቈርጣችሁ አምጡ፤ ቤተ መቅደሱን እንደገና አድሳችሁ ሥሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ብሎኝ እመሰገንበታለሁ። “እናንተማ ብዙ መከር ለመሰብሰብ ዐቅዳችሁ ነበር፤ ነገር ግን ጥቂት ሆነ፤ ያንኑንም ወደ ቤት ባስገባችሁ ጊዜ እኔ እፍ ስላልኩበት ጠፋ፤ ይህንንስ ያደረግኹት ለምን ይመስላችኋል? እኔ ይህን ያደረግኹት፥ ከእናንተ እያንዳንዱ ቤቱን አስጊጦ እየሠራ የእኔ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ ሆኖ በመቅረቱ ነው። ዝናብ የማይዘንብበትና ቡቃያ የማይበቅልበትም ምክንያት ይኸው ነው። እነሆ በዚህ ምክንያት በተራሮች ላይ በእህል፥ በወይን፥ በዘይት፥ ምድር በምታበቅለው ሁሉ ላይ፥ በሰዎችና በእንስሶች፥ በሥራቸውም ውጤት ሁሉ ላይ ድርቅን አመጣለሁ።” የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና ሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ተርፈው ከስደት ከተመለሱት ሕዝብ ጋር ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ቃልና፥ እግዚአብሔር የላከው ስለ ሆነ በነቢዩ ሐጌ አማካይነት ለተላከው መልእክት ታዛዦች ሆኑ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ። የእግዚአብሔር መልእክተኛ የሆነው ሐጌ ለሕዝቡ “ ‘እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ’ ይላል እግዚአብሔር” ሲል የእግዚአብሔርን መልእክት አስተላለፈ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የይሁዳ ገዢ የሆነውን የሰላትያልን ልጅ ዘሩባቤልን፥ ሊቀ ካህናቱን የኢዮሴዴቅን ልጅ ኢያሱንና ተርፈው ከስደት የተመለሱትን ሰዎች ሁሉ መንፈስ አነሣሣ፤ እነርሱም የአምላካቸውን የሠራዊትን ጌታ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመሩ። ይህም የሆነው ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመትና ስድስተኛው ወር በገባ በሃያ አራተኛው ቀን ነበር።