ሐጌ 1:3-15
ሐጌ 1:3-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የእግዚአብሔርም ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤ “ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ፣ እናንተ ራሳችሁ በተዋቡ ቤቶቻችሁ ውስጥ ለመኖር ጊዜው ነውን?” ስለዚህ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “እስቲ መንገዳችሁን ልብ በሉ፤ ብዙ ዘራችሁ፤ ነገር ግን ያጨዳችሁት ጥቂት ነው። በላችሁ፤ ግን አልጠገባችሁም። ጠጣችሁ፤ ግን አልረካችሁም። ለበሳችሁ፤ ግን አልሞቃችሁም። ደመወዝን ተቀበላችሁ፤ ግን በቀዳዳ ኰረጆ የማስቀመጥ ያህል ነው።” እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “እስቲ መንገዳችሁን ልብ በሉ፤ ወደ ተራራ ውጡ፤ ዕንጨት አምጡ፤ ቤቱን ሥሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፤ እከበርበታለሁም” ይላል እግዚአብሔር። ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ብዙ ተስፋ አደረጋችሁ፤ ያገኛችሁት ግን ጥቂት ነው፤ ወደ ቤት ያስገባችሁትንም እኔ እፍ አልሁበት፤ ይህ የሆነው ለምን ይመስላችኋል? የእኔ ቤት ፈርሶ እያለ ሁላችሁም የራሳችሁን ቤት ለመሥራት ስለ ሮጣችሁ ነው፤ ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ሰማያት ጠል ከለከሉ፤ ምድርም ፍሬዋን ነሣች። እኔም በዕርሻዎችና በተራሮች፣ በእህሉና በአዲሱ ወይን ጠጅ፣ በዘይቱና ምድር በምታፈራው ሁሉ፣ በሰውና በእንስሳ፣ በእጆቻችሁም ሥራ ላይ ድርቅ አመጣሁ።” ከዚህ በኋላ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፣ ሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፣ ከምርኮ የተረፉትም ሕዝብ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ድምፅ፣ የነቢዩንም የሐጌን መልእክት ሰሙ፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ልኮታልና። ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ። ቀጥሎም የእግዚአብሔር መልእክተኛ ሐጌ፣ ይህን የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ” ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ እግዚአብሔር የይሁዳን ገዥ፣ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፣ የሊቀ ካህናቱን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስና ከምርኮ የተረፈውን ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አነሣሣ፤ እነርሱም መጥተው የአምላካቸውን የእግዚአብሔር ጸባኦት ቤት መሥራት ጀመሩ። ይህ የሆነውም ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር፣ በሃያ አራተኛው ቀን ነበር።
ሐጌ 1:3-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔርም ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፣ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፣ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፣ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፣ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ወደ ተራራው ውጡ፥ እንጨትንም አምጡ፥ ቤቱንም ሥሩ፣ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፥ እኔም እመሰገናለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ብዙ ነገርን ተስፋ አደረጋችሁ፥ እነሆም፥ ጥቂት ሆነ፣ ወደ ቤትም ባገባችሁት ጊዜ እፍ አልሁበት። ይህ ስለ ምንድር ነው? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ሁሉ ወደ እየቤታችሁ እየሮጣችሁ የእኔ ቤት ፈርሶ ስለ ተቀመጠ ነው። ስለዚህ ሰማያት በላያችሁ ጠልን ከልክለዋል፥ ምድሪቱም ፍሬዋን ከልክላለች። እኔም በምድርና በተራሮች፥ በእህልና በወይንም፥ በዘይትና ምድርም በምታበቅለው ላይ፥ በሰዎችና በእንስሶችም ላይ፥ እጅም በሚደክምበት ሁሉ ላይ ድርቅን ጠርቻለሁ። የሰላትያልም ልጅ ዘሩባቤል፥ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ሕዝብ ሁሉ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ድምፅ የነቢዩንም የሐጌን ቃል፥ አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ላከው ሁሉ ሰሙ፣ ሕዝቡም በእግዚአብሔር ፊት ፈሩ። የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ሐጌ በእግዚአብሔር መልእክት ሕዝቡን፦ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር ብሎ ተናገረ። እግዚአብሔርም የይሁዳን አለቃ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፥ የታላቁንም ካህን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስ፥ የቀሩትንም ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አስነሣ፣ በንጉሡም በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት በስድስተኛው ወር ከወሩም በሀያ አራተኛው ቀን መጡ፥ የአምላካቸውንም የሠራዊትን ጌታ የእግዚአብሔርን ቤት ሠሩ።
ሐጌ 1:3-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእግዚአብሔርም ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? አሁንም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፥ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፥ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፥ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፥ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ወደ ተራራው ውጡ፥ እንጨትንም አምጡ፥ ቤቱንም ሥሩ፥ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፥ እኔም እመሰገናለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። እናንተ ብዙ ነገርን ተስፋ አደረጋችሁ፥ እነሆም፥ ጥቂት ሆነ፥ ወደ ቤትም ባገባችሁት ጊዜ እፍ አልሁበት። ይህ ስለ ምንድር ነው? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። እናንተ ሁሉ ወደ እየቤታችሁ እየሮጣችሁ የእኔ ቤት ፈርሶ ስለ ተቀመጠ ነው። ስለዚህ ሰማያት በላያችሁ ጠልን ከልክለዋል፥ ምድሪቱም ፍሬዋን ከልክላለች። እኔም በምድርና በተራሮች፥ በእህልና በወይንም፥ በዘይትና ምድርም በምታበቅለው ላይ፥ በሰዎችና በእንስሶችም ላይ፥ እጅም በሚደክምበት ሁሉ ላይ ድርቅን ጠርቻለሁ። የሰላትያልም ልጅ ዘሩባቤል፥ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ሕዝብ ሁሉ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ድምፅ የነቢዩንም የሐጌን ቃል፥ አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ላከው ሁሉ ሰሙ፥ ሕዝቡም በእግዚአብሔር ፊት ፈሩ። የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ሐጌ በእግዚአብሔር መልእክት ሕዝቡን፦ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር ብሎ ተናገረ። እግዚአብሔርም የይሁዳን አለቃ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፥ የታላቁንም ካህን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስ፥ የቀሩትንም ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አስነሣ፥ በንጉሡም በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት በስድስተኛው ወር ከወሩም በሀያ አራተኛው ቀን መጡ፥ የአምላካቸውንም የሠራዊትን ጌታ የእግዚአብሔርን ቤት ሠሩ።
ሐጌ 1:3-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህም እግዚአብሔር በነቢዩ በሐጌ አማካይነት ለሕዝቡ የተናገረው ቃል የሚከተለው ነው፤ “ሕዝቤ ሆይ! የእኔ ቤት ፈርሶ ሳለ፥ እናንተ ተውበው በተሠሩ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? ያላችሁበትን ሁኔታ አስቡ። እነሆ ብዙ ዘርታችሁ ጥቂት ሰበሰባችሁ፤ ትበላላችሁ፤ ነገር ግን አትጠግቡም፤ ትጠጣላችሁ፤ ነገር ግን አትረኩም፤ ደራርባችሁ ትለብሳላችሁ፤ ነገር ግን አይሞቃችሁም፤ ሠርታችሁ የምታገኙት ደመወዝ ስለማይበረክትላችሁ፥ በቀዳዳ ኪስ ውስጥ የማኖር ያኽል ይሆናል። ያላችሁበትን ሁኔታ አስቡ። በሉ አሁን ወደ ኰረብቶች ውጡ፤ እንጨትም ቈርጣችሁ አምጡ፤ ቤተ መቅደሱን እንደገና አድሳችሁ ሥሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ብሎኝ እመሰገንበታለሁ። “እናንተማ ብዙ መከር ለመሰብሰብ ዐቅዳችሁ ነበር፤ ነገር ግን ጥቂት ሆነ፤ ያንኑንም ወደ ቤት ባስገባችሁ ጊዜ እኔ እፍ ስላልኩበት ጠፋ፤ ይህንንስ ያደረግኹት ለምን ይመስላችኋል? እኔ ይህን ያደረግኹት፥ ከእናንተ እያንዳንዱ ቤቱን አስጊጦ እየሠራ የእኔ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ ሆኖ በመቅረቱ ነው። ዝናብ የማይዘንብበትና ቡቃያ የማይበቅልበትም ምክንያት ይኸው ነው። እነሆ በዚህ ምክንያት በተራሮች ላይ በእህል፥ በወይን፥ በዘይት፥ ምድር በምታበቅለው ሁሉ ላይ፥ በሰዎችና በእንስሶች፥ በሥራቸውም ውጤት ሁሉ ላይ ድርቅን አመጣለሁ።” የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና ሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ተርፈው ከስደት ከተመለሱት ሕዝብ ጋር ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ቃልና፥ እግዚአብሔር የላከው ስለ ሆነ በነቢዩ ሐጌ አማካይነት ለተላከው መልእክት ታዛዦች ሆኑ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ። የእግዚአብሔር መልእክተኛ የሆነው ሐጌ ለሕዝቡ “ ‘እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ’ ይላል እግዚአብሔር” ሲል የእግዚአብሔርን መልእክት አስተላለፈ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የይሁዳ ገዢ የሆነውን የሰላትያልን ልጅ ዘሩባቤልን፥ ሊቀ ካህናቱን የኢዮሴዴቅን ልጅ ኢያሱንና ተርፈው ከስደት የተመለሱትን ሰዎች ሁሉ መንፈስ አነሣሣ፤ እነርሱም የአምላካቸውን የሠራዊትን ጌታ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመሩ። ይህም የሆነው ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመትና ስድስተኛው ወር በገባ በሃያ አራተኛው ቀን ነበር።
ሐጌ 1:3-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የጌታ ቃል በነቢዩ በሐጌ እጅ እንዲህ ሲል መጣ፦ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በታጠሩ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? አሁንም የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልሰከራችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ለማስቀመጥ ደመወዙን ተቀበለ። የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ። በእርሱ ደስ እንዲለኝና እንድከበርበት፥ ወደ ተራራው ውጡ፥ እንጨትን አምጡ፥ ቤቱንም ሥሩ። ይላል ጌታ። እናንተ ብዙ ነገርን ፈልጋችሁ፥ እነሆ ጥቂት ሆነ፤ ወደ ቤትም ባገባችሁት ጊዜ እፍ አልሁበት። በምን ምክንያት? ይላል የሠራዊት ጌታ። ምክንያቱም እናንተ ሁሉ ወደ እየቤታችሁ እየሮጣችሁ የእኔ ቤት ስለፈረሰ ነው። ስለዚህ ሰማያት በላያችሁ ጠልን ከልክለዋል፥ ምድሪቱም የምታበቅለውን ከልክላለች። እኔም በምድሪቱና በተራሮች፥ በእህልና በአዲሱ ወይን፥ በዘይትና ምድር በምታበቅለው ላይ፥ በሰዎችና በከብቶች ላይ፥ እጅም በሚደክምበት ሁሉ ላይ ድርቅን ጠርቻለሁ። የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና ታላቁ ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩትም ሕዝብ ሁሉ የአምላካቸውን የጌታን ድምፅ የነቢዩንም የሐጌን ቃል ሰሙ፥ አምላካቸው ጌታ ልኮታልና፤ ሕዝቡም በጌታ ፊት ፈሩ። የጌታ መልእክተኛ ሐጌ በጌታ መልእክት ሕዝቡን፦ “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ይላል ጌታ” ብሎ ተናገረ። ጌታም የይሁዳን ገዢ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፥ የታላቁን ካህን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስና የቀሩትንም ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አስነሣ፤ መጥተውም የአምላካቸውን የሠራዊትን ጌታ ቤት ሠሩ። ይህም በንጉሡ በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት፥ በስድስተኛው ወር ከወሩም በሀያ አራተኛው ቀን ነው።