የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሐጌ 1

1
እግዚአብሔር ስለ ቤተ መቅደሱ መታደስ የሰጠው ትእዛዝ
1ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ ስድስተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን፥ እግዚአብሔር በነቢዩ አማካይነት በሐጌ ተናገረ የተናገረውም የይሁዳ ገዢ ለነበረው ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤልና ሊቀ ካህናት ለነበረው ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ ነው። #ዕዝ. 4፥24—5፥2፤ 6፥14።
2የሠራዊት አምላክ “ይህ ሕዝብ ‘ቤተ መቅደሱ እንደገና ታድሶ የሚሠራበት ጊዜ ገና አልደረሰም’ ይላል፤” 3ስለዚህም እግዚአብሔር በነቢዩ በሐጌ አማካይነት ለሕዝቡ የተናገረው ቃል የሚከተለው ነው፤ 4“ሕዝቤ ሆይ! የእኔ ቤት ፈርሶ ሳለ፥ እናንተ ተውበው በተሠሩ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው ነውን? 5ያላችሁበትን ሁኔታ አስቡ። 6እነሆ ብዙ ዘርታችሁ ጥቂት ሰበሰባችሁ፤ ትበላላችሁ፤ ነገር ግን አትጠግቡም፤ ትጠጣላችሁ፤ ነገር ግን አትረኩም፤ ደራርባችሁ ትለብሳላችሁ፤ ነገር ግን አይሞቃችሁም፤ ሠርታችሁ የምታገኙት ደመወዝ ስለማይበረክትላችሁ፥ በቀዳዳ ኪስ ውስጥ የማኖር ያኽል ይሆናል። 7ያላችሁበትን ሁኔታ አስቡ። 8በሉ አሁን ወደ ኰረብቶች ውጡ፤ እንጨትም ቈርጣችሁ አምጡ፤ ቤተ መቅደሱን እንደገና አድሳችሁ ሥሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ብሎኝ እመሰገንበታለሁ።
9“እናንተማ ብዙ መከር ለመሰብሰብ ዐቅዳችሁ ነበር፤ ነገር ግን ጥቂት ሆነ፤ ያንኑንም ወደ ቤት ባስገባችሁ ጊዜ እኔ እፍ ስላልኩበት ጠፋ፤ ይህንንስ ያደረግኹት ለምን ይመስላችኋል? እኔ ይህን ያደረግኹት፥ ከእናንተ እያንዳንዱ ቤቱን አስጊጦ እየሠራ የእኔ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ ሆኖ በመቅረቱ ነው። 10ዝናብ የማይዘንብበትና ቡቃያ የማይበቅልበትም ምክንያት ይኸው ነው። 11እነሆ በዚህ ምክንያት በተራሮች ላይ በእህል፥ በወይን፥ በዘይት፥ ምድር በምታበቅለው ሁሉ ላይ፥ በሰዎችና በእንስሶች፥ በሥራቸውም ውጤት ሁሉ ላይ ድርቅን አመጣለሁ።”
የሕዝቡ ለእግዚአብሔር መታዘዝ
12የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና ሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ተርፈው ከስደት ከተመለሱት ሕዝብ ጋር ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ቃልና፥ እግዚአብሔር የላከው ስለ ሆነ በነቢዩ ሐጌ አማካይነት ለተላከው መልእክት ታዛዦች ሆኑ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ። 13የእግዚአብሔር መልእክተኛ የሆነው ሐጌ ለሕዝቡ “ ‘እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ’ ይላል እግዚአብሔር” ሲል የእግዚአብሔርን መልእክት አስተላለፈ። 14ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር የይሁዳ ገዢ የሆነውን የሰላትያልን ልጅ ዘሩባቤልን፥ ሊቀ ካህናቱን የኢዮሴዴቅን ልጅ ኢያሱንና ተርፈው ከስደት የተመለሱትን ሰዎች ሁሉ መንፈስ አነሣሣ፤ እነርሱም የአምላካቸውን የሠራዊትን ጌታ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመሩ። 15ይህም የሆነው ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመትና ስድስተኛው ወር በገባ በሃያ አራተኛው ቀን ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ