የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሐጌ 1:3-15

ሐጌ 1:3-15 NASV

የእግዚአብሔርም ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤ “ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ፣ እናንተ ራሳችሁ በተዋቡ ቤቶቻችሁ ውስጥ ለመኖር ጊዜው ነውን?” ስለዚህ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “እስቲ መንገዳችሁን ልብ በሉ፤ ብዙ ዘራችሁ፤ ነገር ግን ያጨዳችሁት ጥቂት ነው። በላችሁ፤ ግን አልጠገባችሁም። ጠጣችሁ፤ ግን አልረካችሁም። ለበሳችሁ፤ ግን አልሞቃችሁም። ደመወዝን ተቀበላችሁ፤ ግን በቀዳዳ ኰረጆ የማስቀመጥ ያህል ነው።” እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “እስቲ መንገዳችሁን ልብ በሉ፤ ወደ ተራራ ውጡ፤ ዕንጨት አምጡ፤ ቤቱን ሥሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፤ እከበርበታለሁም” ይላል እግዚአብሔር። ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ብዙ ተስፋ አደረጋችሁ፤ ያገኛችሁት ግን ጥቂት ነው፤ ወደ ቤት ያስገባችሁትንም እኔ እፍ አልሁበት፤ ይህ የሆነው ለምን ይመስላችኋል? የእኔ ቤት ፈርሶ እያለ ሁላችሁም የራሳችሁን ቤት ለመሥራት ስለ ሮጣችሁ ነው፤ ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ሰማያት ጠል ከለከሉ፤ ምድርም ፍሬዋን ነሣች። እኔም በዕርሻዎችና በተራሮች፣ በእህሉና በአዲሱ ወይን ጠጅ፣ በዘይቱና ምድር በምታፈራው ሁሉ፣ በሰውና በእንስሳ፣ በእጆቻችሁም ሥራ ላይ ድርቅ አመጣሁ።” ከዚህ በኋላ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፣ ሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፣ ከምርኮ የተረፉትም ሕዝብ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ድምፅ፣ የነቢዩንም የሐጌን መልእክት ሰሙ፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ልኮታልና። ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ። ቀጥሎም የእግዚአብሔር መልእክተኛ ሐጌ፣ ይህን የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ” ይላል እግዚአብሔር። ስለዚህ እግዚአብሔር የይሁዳን ገዥ፣ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፣ የሊቀ ካህናቱን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስና ከምርኮ የተረፈውን ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አነሣሣ፤ እነርሱም መጥተው የአምላካቸውን የእግዚአብሔር ጸባኦት ቤት መሥራት ጀመሩ። ይህ የሆነውም ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር፣ በሃያ አራተኛው ቀን ነበር።