ኦሪት ዘፍጥረት 39:13-23

ኦሪት ዘፍጥረት 39:13-23 አማ05

እርስዋም ልብሱን በእጅዋ ላይ ትቶ ከቤት ሸሽቶ መውጣቱን በተመለከተች ጊዜ፥ አገልጋዮችዋን ጠርታ እንዲህ አለቻቸው፤ “እነሆ፥ ባለቤቴ ያመጣው ይህ ዕብራዊ ሊያዋርደን ነበር፤ ወዳለሁበት ክፍል ገብቶ ሊደፍረኝ ሞከረ፤ እኔ ግን ድምፄን ከፍ አድርጌ ጮኽኩ። ርዳታ ለማግኘትም መጮኼን በሰማ ጊዜ ልብሱን አጠገቤ ትቶ ከቤት ሸሽቶ ወጣ።” የዮሴፍ አሳዳሪ እስኪመጣ ድረስ ልብሱን በእርስዋ ዘንድ አቈየችው። በመጣም ጊዜ የሆነውን ታሪክ እንዲህ ስትል ዘርዝራ ነገረችው፥ “አንተ ወደዚህ ያመጣኸው ዕብራዊ አገልጋይ ወዳለሁበት ክፍል ገብቶ ሊያዋርደኝ ነበር። ነገር ግን ርዳታ ለማግኘት ድምፄን ከፍ አድርጌ በጮኽኩ ጊዜ ልብሱን አጠገቤ ትቶ ከቤት ሸሽቶ ወጣ።” ሚስቱ “የአንተ አገልጋይ እንዲህ አደረገኝ” ብላ የነገረችውን ታሪክ በሰማ ጊዜ የዮሴፍ አሳዳሪ እጅግ ተቈጣ። ስለዚህ ዮሴፍን ወስዶ የንጉሡ እስረኞች ወዳሉበት እስር ቤት አስገባው። ነገር ግን ዮሴፍ በእስር ቤት በነበረበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሆኖ ዘላቂ ፍቅሩን አሳየው፤ በእስር ቤቱ አዛዥ ዘንድ ባለሟልነትን እንዲያገኝ አደረገው። በዚህ ዐይነት በእስረኞቹ ሁሉ ላይና በእስር ቤቱ ውስጥ በሚደረገው ነገር ሁሉ ላይ ኀላፊ አደረገው። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ሆኖ የሚያደርገው ነገር ሁሉ እንዲቃናለት ስላደረገ የእስር ቤቱ አዛዥ በዮሴፍ ቊጥጥር ሥር በነበረው ነገር ምንም ሐሳብ አልነበረበትም።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}