ኦሪት ዘፍጥረት 38:1-26

ኦሪት ዘፍጥረት 38:1-26 አማ05

በዚያም ወራት ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ሒራ ወደሚሉት ዐዱላማዊ ሰው ዘንድ ሄዶ መኖሪያውን እዚያ አደረገ። እዚያም ይሁዳ የከነዓናዊውን የሹዓን ሴት ልጅ አየ፤ እርስዋንም አግብቶ ወደርስዋ ገባ። እርስዋም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው። እንደገናም ፀነሰችና ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም ኦናን ብላ ጠራችው፤ እንደገናም ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም ሴላ ብላ ጠራችው፤ እርሱንም የወለደችው ይሁዳ አክዚብ በሚባል ቦታ በሚኖርበት ጊዜ ነው። ይሁዳ የመጀመሪያ ልጁን ዔርን ትዕማር ከምትባል ልጃገረድ ጋር አጋባው። ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሰው ስለ ነበረ፥ እግዚአብሔር በሞት ቀሠፈው። ይሁዳ የዔርን ወንድም ኦናንን “ሂድና ወደ ወንድምህ ሚስት ገብተህ በደንቡ መሠረት ለወንድምህ መጠሪያ የሚሆን ዘር አስቀርለት” አለው። ኦናን የሚወለዱት ልጆች የእርሱ ያለመሆናቸውን በማወቁ ወደ ወንድሙ ሚስት ሲገባ ዘሩን ወደ ምድር ያፈሰው ነበር፤ በዚህ ዐይነት በወንድሙ ስም ልጆች እንዳይወለዱ አደረገ። ይህን በማድረጉ እግዚአብሔርን ስላሳዘነ እግዚአብሔር እርሱንም በሞት ቀሠፈው። ከዚህ በኋላ ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን “ልጄ ሴላ እስከሚያድግበት ጊዜ ድረስ ሂጂና በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ኑሪ” አላት። ይህንንም ያለው እንደ ወንድሞቹ ይሞትብኛል ብሎ ስለ ሰጋ ነበር፤ ስለዚህ ትዕማር ሄዳ በአባቷ ቤት ተቀመጠች። በርከት ካሉ ዓመቶች በኋላ የሴዋ ልጅ የሆነችው የይሁዳ ሚስት ሞተች፤ ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከወዳጁ ከዐዱላማዊው ከሒራ ጋር በጎቹን ወደሚሸልቱ ሰዎች ወደ ቲምና ሄደ። ሰዎቹም ለትዕማር “አማትሽ በጎቹን ለማሸለት ወደ ቲምና ይሄዳል” ብለው ነገሩአት። ስለዚህ ትዕማር የመበለትነት ልብሷን ለውጣ ፊቷን በሻሽ ሸፈነች፤ ወደ ቲምና በሚወስደው መንገድ ዳር በዔናይም ደጅ ተቀመጠች፤ ይህንንም ያደረገችው ሴላ አድጎ ሳለ ለእርሱ በሚስትነት እንድትሰጥ አለመፈቀዱን ስለ ተረዳች ነው። ፊቷን በሻሽ ሸፍና ስለ ነበር ይሁዳ ባያት ጊዜ አመንዝራ ሴት መሰለችው። ምራቱ እንደ ሆነች ሳያውቅ እርስዋ ወደተቀመጠችበት ወደ መንገድ ዳር ወጣ አለና “እባክሽ ወደ አንች እንድገባ ፍቀጂልኝ” ብሎ ጠየቃት። እርስዋ “ፈቃድህን ብፈጽም ምን ትሰጠኛለህ?” አለችው። እርሱም “ከመንጋዎቼ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እርስዋም “እሺ እንግዲያውስ ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ መያዣ የሚሆን ነገር ስጠኝ” አለችው። እርሱም “ታዲያ፥ መያዣ የሚሆን ነገር ምን ልስጥሽ?” አላት። እርስዋም “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያውና ይህን የያዝከውን በትር ስጠኝ” አለችው። ስለዚህ የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና ወደ እርስዋ ገባ፤ እርስዋም ፀነሰችለት ከዚያ በኋላ ሻሽዋን ከፊቷ ላይ አንሥታ የመበለትነት ልብሷን እንደገና ለበሰች። ይሁዳ በመያዥያ መልክ የሰጣትን ነገሮች ለማስመለስ የፍየል ጠቦት በዐዱላማዊው ሰው እጅ ወደ ሴትዮዋ ላከ፤ ሰውየው ግን ሊያገኛት አልቻለም። ሰውየውም እዚያ የሚኖሩትን ሰዎች “በዔናይም ደጅ በመንገድ ዳር የነበረችው አመንዝራ ሴት ወዴት ሄደች?” ብሎ ጠየቀ። ሰዎቹም “በዚህ አካባቢ እንደዚህ ያለች አመንዝራ ሴት የለችም” አሉት። ስለዚህ ሰውየው ወደ ይሁዳ ተመልሶ ሄደና “ላገኛት አልቻልኩም፤ በዚያ የሚኖሩትም ሰዎች ‘እንደዚህ ያለች አመንዝራ ሴት እዚህ የለችም’ አሉኝ” ብሎ ነገረው። ይሁዳም “እንግዲህ ጠቦቱን ልኬላት ነበር፤ ነገር ግን ልታገኛት አልቻልክም፤ ስለዚህ ሰዎች መሳቂያ እንዳያደርጉን የወሰደችውን መያዣ እዚያው ታስቀረው” አለ። በሦስተኛው ወር ገደማ ሰዎች “ምራትህ ትዕማር የዝሙት ሥራ ፈጸመች፤ ከዚህም የተነሣ ፀንሳለች” ብለው ለይሁዳ ነገሩት። ይሁዳም “ወደ ውጪ አውጥታችሁ በእሳት አቃጥላችሁ ግደሉአት” አለ። እርስዋም ተይዛ ውጪ በምትወጣበት ጊዜ “እኔ የፀነስኩት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው፤ ይህን የማኅተም ቀለበት ከነማሰሪያውና ይህንንም በትር ተመልክተህ የማን እንደ ሆኑ ዕወቅ” ብላ ለዐማቷ ለይሁዳ ላከችለት። ይሁዳም ዕቃዎቹ የማን እንደ ሆኑ ዐውቆ “ከልጄ ከሴላ ጋር ስላላጋባኋት እርስዋ ከእኔ ይልቅ ትክክለኛ ሆና ተገኘች” አለ፤ ወደ እርስዋም ዳግመኛ አልገባም።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}