በዚያም ወራት ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ፣ ኤራ ወደ ተባለ ዓዶላማዊ ሰው ወረደ፤ እርሱም ዘንድ ለመኖር ቤቱ ገባ። እዚያም ሳለ፣ ይሁዳ የከነዓናዊውን የሹዓን ሴት ልጅ አየ፤ እርሷንም አግብቶ ዐብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙም ዔር ተባለ። እንደ ገናም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙን አውናን አለችው። አሁንም ደግማ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሴሎም ብላ አወጣችለት፤ እርሱንም የወለደችው ክዚብ በተባለ ቦታ ነበር። ይሁዳ የበኵር ልጁን ዔርን፣ ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው። የይሁዳ የበኵር ልጅ ዔር ግን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበር፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው። በዚህ ጊዜ ይሁዳ አውናንን፣ “ዋርሳዋ እንደ መሆንህ ከወንድምህ ሚስት ጋራ ሩካቤ ሥጋ በመፈጸም የወንድምህን ስም የሚያስጠራለት ዘር ተካለት” አለው። አውናን ግን የሚወለደው ልጅ የርሱን ስም የሚያስጠራ እንደማይሆን ስላወቀ፣ ከወንድሙ ሚስት ጋራ ሩካቤ ሥጋ በፈጸመ ቍጥር የወንድሙንም ስም የሚያስጠራ ልጅ እንዳይወልድ ዘሩን በምድር ላይ ያፈስስ ነበር። ይህም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድራጎት ሆኖ ስለ ተገኘ፣ እርሱንም እግዚአብሔር በሞት ቀሠፈው። ከዚያም ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን፣ “ልጄ ሴሎም ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ ወደ አባትሽ ቤት ሄደሽ መበለት ሆነሽ ብትኖሪ ይሻላል” አላት። ይህን ያለውም፣ ሴሎም እንደ ወንድሞቹ ተቀሥፎ ይሞትብኛል ብሎ ስለ ሠጋ ነበር። ትዕማርም እንዳላት ሄደች፤ በአባቷም ቤት ተቀመጠች። ከብዙ ጊዜ በኋላ የሹዓ ልጅ፣ የይሁዳ ሚስት ሞተች። ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከዓዶላማዊው ከኤራ ጋራ የበጎቹን ጠጕር የሚሸልቱ ሰዎች ወዳሉበት ወደ ተምና ሄደ። ሰዎቹም ለትዕማር፣ “ዐማትሽ የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱ ሰዎች ዘንድ ወደ ተምና እየሄደ ነው” አሏት። ይህን እንደ ሰማች የመበለትነት ልብሷን አውልቃ፣ ማንነቷ እንዳይታወቅ ፊቷን በሻሽ ተከናንባ ወደ ተምና በሚወስደው መንገድ ዳር ባለች ኤናይም በተባለች ከተማ መግቢያ ላይ ተቀመጠች፤ ይህን ያደረገችው፣ ሴሎም ለአካለ መጠን ቢደርስም፣ እርሷን እንዲያገባ አባቱ አለመፈለጉን ስላወቀች ነው። ፊቷ በሻሽ ተሸፋፍኖ ሲያያት፣ ይሁዳ ዝሙት ዐዳሪ መሰለችው። ምራቱ መሆኗን ባለማወቁ፣ እርሷ ወዳለችበት ወደ መንደሩ ዳር ጠጋ ብሎ፣ “እባክሽ ዐብሬሽ ልተኛ” አላት። እርሷም፣ “ዐብሬህ ብተኛ ምን ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። “ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እርሷም መልሳ፣ “ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ ምን መያዣ ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። “ታዲያ ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርሷም፣ “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያው፣ እንደዚሁም ይህን በትርህን ስጠኝ” አለችው። የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና ዐብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች። ከዚያም ወደ መኖሪያዋ ተመልሳ፣ ሻሿን አውልቃ እንደ ወትሮዋ የመበለት ልብሷን ለበሰች። ይሁዳ በመያዣ ስም የሰጣትን ዕቃዎች ለማስመለስ የፍየሉን ጠቦት በዓዶላማዊ ወዳጁ እጅ ላከላት፣ መልእክተኛው ግን ሴትዮዋን ሊያገኛት አልቻለም። “በኤናይም ከተማ መግቢያ ከመንገዱ ዳር የነበረች ያቺ ዝሙት ዐዳሪ የት ደረሰች?” ሲል ጠየቃቸው። ሰዎቹም፣ “በዚህ አካባቢ ኧረ ምንም ዝሙት ዐዳሪ ታይታ አትታወቅም” አሉት። መልእክተኛውም ወደ ይሁዳ ተመልሶ፣ “ሴቲቱን ላገኛት አልቻልሁም፤ ነዋሪዎቹም ‘በዚህ አካባቢ እንደዚህች ያለች ዝሙት ዐዳሪ የለችም’ አሉኝ” ብሎ ነገረው። ይሁዳም፣ “እንግዲህ መያዣውን እንደ ያዘች ትቅር፣ አለዚያ መሣቂያ እንሆናለን። ለነገሩማ ይህን ፍየል ላክሁ፤ አንተም ፈልገህ አላገኘሃትም” አለ። ከሦስት ወር ያህል በኋላ፣ “ምራትህ ትዕማር ዘማዊ ሆናለች፤ ከዚህም የተነሣ አርግዛለች” ተብሎ ለይሁዳ ተነገረው። ይሁዳም፣ “አውጧትና በእሳት ተቃጥላ ትሙት” አለ። እርሷም ተይዛ በምትወሰድበት ጊዜ ለዐማቷ፣ “እኔ ያረገዝሁት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው” ስትል ላከችበት፤ ደግሞም፣ “የማኅተሙ ቀለበት ከነማንጠልጠያውና በትሩ የማን እንደ ሆነ እስኪ ተመልከት” አለችው። ይሁዳም ዕቃዎቹን ዐውቆ፣ “ልጄ ሴሎም እንዲያገባት ባለማድረጌ፣ እርሷ ከእኔ ይልቅ ትክክል ናት” አለ። ከዚያም በኋላ ከርሷ ጋራ አልተኛም።
ዘፍጥረት 38 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 38
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 38:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች