ያዕቆብ ቀና ብሎ ሲመለከት፥ ዔሳው አራት መቶ ሰዎችን አስከትሎ ሲመጣ አየ፤ ያዕቆብም ልጆቹን ከልያ፥ ከራሔልና ከሁለቱ ሴቶች አገልጋዮቹ ጋር ከፋፈላቸው። በመጀመሪያ ሁለቱን ሴቶች አገልጋዮቹንና ልጆቻቸውን አስቀደመ፤ ቀጥሎ ልያንና ልጆችዋን አስከተለ፤ በመጨረሻም ራሔልንና ዮሴፍን ከሁሉ በኋላ አደረገ። ያዕቆብ ከሁሉ ቀድሞ ተጓዘ፤ ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ሲቀርብ ወደ መሬት በመጐንበስ ሰባት ጊዜ እጅ ነሣ፤ ዔሳው ግን ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጠ፤ በአንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ዕቅፍ አድርጎ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። ዔሳው በዙሪያው ተመልክቶ ሴቶቹንና ልጆቹን ባየ ጊዜ “እነዚህ ሁሉ ከአንተ ጋር ያሉ ሰዎች የማን ናቸው?” አለ። ያዕቆብም “ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ እግዚአብሔር በቸርነቱ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” ሲል መለሰ። ከዚህ በኋላ ሴቶች አገልጋዮቹ ከልጆቻቸው ጋር መጥተው እጅ ነሡ። ቀጥሎም ልያና ልጆችዋ ቀርበው እጅ ነሡ፤ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል ቀርበው እጅ ነሡ። ዔሳውም “እፊት እፊትስ እየተነዳ ሲሄድ ያየሁት የእንስሶች መንጋ ምንድን ነው?” አለ። ያዕቆብም “ጌታዬ ሆይ፥ እርሱ በአንተ ፊት ሞገስ እንዳገኝ የላክሁልህ ነው” አለ። ዔሳውም “ወንድሜ ሆይ፥ እኔ በቂ ሀብት አለኝ፤ የአንተ ለራስህ ይሁን” አለው። ያዕቆብ ግን “እንዲህስ አይሁን፤ በእርግጥ የምትወደኝ ከሆነ እባክህ ስጦታዬን ተቀበል፤ ፍቅር ስላሳየኸኝ፥ የአንተን ፊት ማየት የእግዚአብሔርን ፊት እንደማየት ያኽል እቈጥረዋለሁ። ስለዚህ እባክህ ይህን ያቀረብኩልህን ስጦታ ተቀበለኝ፤ እግዚአብሔር በቸርነቱ የሚያስፈልገኝን ሁሉ ሰጥቶኛል” አለ። ስጦታውን እንዲቀበለው ያዕቆብ ዔሳውን አጥብቆ ለመነው። እርሱም ተቀበለው። ዔሳውም “እንግዲህ እንሂድ፤ እኔም ከአንተ ቀድሜ እሄዳለሁ” አለ። ያዕቆብም እንዲህ አለ፤ “ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ጌታዬ ታውቃለህ፤ ለሚያጠቡት እንስሶች፥ ለግልገሎቻቸውና ለእንቦሶቻቸው መጠንቀቅ ይኖርብኛል፤ ለአንድ ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ እንስሶቹ በሙሉ ያልቃሉ። ስለዚህ እባክህ ጌታዬ አንተ ቀድመህ ሂድ፤ እኔም በዝግታ እከተልሃለሁ፤ በእንስሶቹና በልጆቹ ዐቅም ልክ እየተራመድኩ በኤዶም እደርስብሃለሁ።” ዔሳውም “እንግዲያውስ ከእኔ ሰዎች ጥቂቶቹን ከአንተ ጋር ላስቀርልህ” አለው። ያዕቆብ ግን “በጌታዬ ፊት ሞገስ ካገኘሁ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልገኝም” አለው። ስለዚህ ዔሳው በዚያኑ ቀን ጒዞውን በመጀመር ወደ ኤዶም ተመለሰ። ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት አመራ፤ እዚያም ለራሱ ቤትና ለከብቶቹም መጠለያ ሠራ፤ ስለዚህ ያ ስፍራ ሱኮት ተባለ። ከመስጴጦምያ በተመለሰ ጊዜ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሴኬም በሰላም ደረሰ፤ እዚያም በከተማይቱ ፊት ለፊት በሚገኘው ሜዳ ላይ ሰፈረ። ድንኳኑን የተከለበትን የሴኬም አባት ከነበረው ከሐሞር ዘሮች ላይ በመቶ ብር ገዛው፤ እዚያም መሠዊያ ሠራና “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር” ብሎ ጠራው።
ኦሪት ዘፍጥረት 33 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 33:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos