ያዕቆብ አሻግሮ ተመለከተ፤ እነሆ ዔሳው አራት መቶ ሰዎች አስከትሎ እየመጣ ነበር። ስለዚህ ልጆቹን ለልያ፣ ለራሔልና ለሁለቱ አገልጋዮች አከፋፈላቸው። ከዚያም ሁለቱን አገልጋዮች ከነልጆቻቸው አስቀደመ፤ ልያንና ልጆቿንም አስከተለ፤ ራሔልንና ዮሴፍን ግን ከሁሉ ኋላ እንዲሆኑ አደረገ። እርሱ ራሱም ቀድሟቸው ሄደ፤ ወንድሙም ዘንድ እስኪደርስ ድረስ ሰባት ጊዜ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ። ዔሳው ግን ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጦ ሄዶ ዐቀፈው፤ በዐንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። ከዚያም ዔሳው ቀና ብሎ ሲመለከት ሴቶቹንና ልጆቹን አየ፤ እርሱም፣ “እነዚህ አብረውህ ያሉት እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀው። ያዕቆብም መልሶ፣ “እነዚህማ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቸርነቱ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለው። በዚህ ጊዜ ሁለቱ ሴት አገልጋዮችና ልጆቻቸው ቀርበው እጅ ነሡ፤ ከዚያም ልያና ልጆቿ መጥተው እጅ ነሡ፤ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል መጡ፤ እነርሱም ቀርበው እጅ ነሡ። ዔሳውም፣ “ወደ እኔ ተነድቶ የመጣው ይህ ሁሉ መንጋ ምንድን ነው?” አለው። እርሱም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ ባገኝ ብዬ ነው” አለው። ዔሳው ግን፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እኔ በቂ አለኝ፤ የራስህን ለራስህ አድርገው” አለው። ያዕቆብም፣ “የለም፣ እንዲህ አይደለም፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ እጅ መንሻዬን ተቀበል፤ በመልካም ሁኔታ ተቀብለኸኝ ፊትህን ማየት መቻሌን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት እንደ ማየት እቈጥረዋለሁ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቸርነቱ አሟልቶ ስለ ሰጠኝ የሚያስፈልገኝ ሁሉ አለኝና ያቀረብሁልህን እጅ መንሻ እባክህ ተቀበለኝ” አለው። ያዕቆብ አጥብቆ ስለ ለመነው፣ ዔሳው እጅ መንሻውን ተቀበለ። ዔሳውም “በል ተነሥና ጕዟችንን እንቀጥል፤ እኔም እሄዳለሁ” አለው። ያዕቆብ ግን እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ፣ እንደምታየው ልጆቹ ይህን ያህል የጠኑ አይደሉም፣ ለሚያጠቡት በጎችና ጥገቶች እንክብካቤ ማድረግ አለብኝ፤ እንስሳቱ ለአንዲት ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ በሙሉ ያልቃሉ። ስለዚህ ጌታዬ፣ አንተ ቀድመኸኝ ሂድ፤ እኔም በምነዳቸው እንስሳትና በልጆቹ ጕዞ ዐቅም ልክ እያዘገምሁ ሴይር ላይ እንገናኛለን።” ዔሳው፣ “እንግዲያስ ከሰዎቼ ጥቂቶቹን ልተውልህ” አለው። ያዕቆብ ግን፣ “ለምን ብለህ ጌታዬ? በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘቴ ብቻ ይበቃኛል” አለው። ስለዚህ ዔሳው በዚሁ ዕለት ወደ ሴይር ለመመለስ ተነሣ። ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት ሄደ፤ እዚያም ለራሱ መጠለያ፣ ለከብቶቹም በረት ሠራ፤ ከዚህም የተነሣ የቦታው ስም ሱኮት ተባለ። ያዕቆብ ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ከተመለሰ በኋላ፣ በከነዓን ወዳለችው ወደ ሴኬም በደኅና ደረሰ፤ በከተማዪቱም ፊት ለፊት ሰፈረ። ድንኳኑን የተከለበትንም ቦታ ከኤሞር ልጆች በመቶ ጥሬ ብር ገዛ፤ ኤሞርም የሴኬም አባት ነበር። በዚያም መሠዊያ አቁሞ፣ ኤል ኤሎሄ እስራኤል ብሎ ጠራው።
ዘፍጥረት 33 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 33
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 33:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos