የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 33

33
ያዕቆብ ከዔሳው ጋር መገናኘቱ
1ያዕቆብ ቀና ብሎ ሲመለከት፥ ዔሳው አራት መቶ ሰዎችን አስከትሎ ሲመጣ አየ፤ ያዕቆብም ልጆቹን ከልያ፥ ከራሔልና ከሁለቱ ሴቶች አገልጋዮቹ ጋር ከፋፈላቸው። 2በመጀመሪያ ሁለቱን ሴቶች አገልጋዮቹንና ልጆቻቸውን አስቀደመ፤ ቀጥሎ ልያንና ልጆችዋን አስከተለ፤ በመጨረሻም ራሔልንና ዮሴፍን ከሁሉ በኋላ አደረገ። 3ያዕቆብ ከሁሉ ቀድሞ ተጓዘ፤ ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ሲቀርብ ወደ መሬት በመጐንበስ ሰባት ጊዜ እጅ ነሣ፤ 4ዔሳው ግን ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጠ፤ በአንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ዕቅፍ አድርጎ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። 5ዔሳው በዙሪያው ተመልክቶ ሴቶቹንና ልጆቹን ባየ ጊዜ “እነዚህ ሁሉ ከአንተ ጋር ያሉ ሰዎች የማን ናቸው?” አለ።
ያዕቆብም “ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ እግዚአብሔር በቸርነቱ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” ሲል መለሰ። 6ከዚህ በኋላ ሴቶች አገልጋዮቹ ከልጆቻቸው ጋር መጥተው እጅ ነሡ። 7ቀጥሎም ልያና ልጆችዋ ቀርበው እጅ ነሡ፤ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል ቀርበው እጅ ነሡ።
8ዔሳውም “እፊት እፊትስ እየተነዳ ሲሄድ ያየሁት የእንስሶች መንጋ ምንድን ነው?” አለ።
ያዕቆብም “ጌታዬ ሆይ፥ እርሱ በአንተ ፊት ሞገስ እንዳገኝ የላክሁልህ ነው” አለ።
9ዔሳውም “ወንድሜ ሆይ፥ እኔ በቂ ሀብት አለኝ፤ የአንተ ለራስህ ይሁን” አለው።
10ያዕቆብ ግን “እንዲህስ አይሁን፤ በእርግጥ የምትወደኝ ከሆነ እባክህ ስጦታዬን ተቀበል፤ ፍቅር ስላሳየኸኝ፥ የአንተን ፊት ማየት የእግዚአብሔርን ፊት እንደማየት ያኽል እቈጥረዋለሁ። 11ስለዚህ እባክህ ይህን ያቀረብኩልህን ስጦታ ተቀበለኝ፤ እግዚአብሔር በቸርነቱ የሚያስፈልገኝን ሁሉ ሰጥቶኛል” አለ። ስጦታውን እንዲቀበለው ያዕቆብ ዔሳውን አጥብቆ ለመነው። እርሱም ተቀበለው።
12ዔሳውም “እንግዲህ እንሂድ፤ እኔም ከአንተ ቀድሜ እሄዳለሁ” አለ።
13ያዕቆብም እንዲህ አለ፤ “ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ጌታዬ ታውቃለህ፤ ለሚያጠቡት እንስሶች፥ ለግልገሎቻቸውና ለእንቦሶቻቸው መጠንቀቅ ይኖርብኛል፤ ለአንድ ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ እንስሶቹ በሙሉ ያልቃሉ። 14ስለዚህ እባክህ ጌታዬ አንተ ቀድመህ ሂድ፤ እኔም በዝግታ እከተልሃለሁ፤ በእንስሶቹና በልጆቹ ዐቅም ልክ እየተራመድኩ በኤዶም እደርስብሃለሁ።”
15ዔሳውም “እንግዲያውስ ከእኔ ሰዎች ጥቂቶቹን ከአንተ ጋር ላስቀርልህ” አለው።
ያዕቆብ ግን “በጌታዬ ፊት ሞገስ ካገኘሁ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልገኝም” አለው። 16ስለዚህ ዔሳው በዚያኑ ቀን ጒዞውን በመጀመር ወደ ኤዶም ተመለሰ። 17ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት አመራ፤ እዚያም ለራሱ ቤትና ለከብቶቹም መጠለያ ሠራ፤ ስለዚህ ያ ስፍራ ሱኮት ተባለ። #33፥17 ሱኮት፦ በዕብራይስጥ “መጠለያ ወይም ዳስ” ማለት ነው።
18ከመስጴጦምያ በተመለሰ ጊዜ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሴኬም በሰላም ደረሰ፤ እዚያም በከተማይቱ ፊት ለፊት በሚገኘው ሜዳ ላይ ሰፈረ። 19ድንኳኑን የተከለበትን የሴኬም አባት ከነበረው ከሐሞር ዘሮች ላይ በመቶ ብር ገዛው፤ #ኢያሱ 24፥32፤ ዮሐ. 4፥5። 20እዚያም መሠዊያ ሠራና “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር” ብሎ ጠራው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ