ኦሪት ዘፍጥረት 29:1-14

ኦሪት ዘፍጥረት 29:1-14 አማ05

ያዕቆብ ጒዞውን ቀጥሎ በስተምሥራቅ ወዳለው አገር ደረሰ፤ እዚያም በሜዳ ላይ አንድ የውሃ ጒድጓድ አየ፤ በሦስት የተከፈሉ የበግ መንጋዎች በጒድጓዱ ዙሪያ ነበሩ፤ መንጋዎቹ ውሃ የሚጠጡት ከዚሁ ጒድጓድ ነበር፤ ጒድጓዱም የሚዘጋበት ድንጋይ ትልቅ ነበር፤ መንጋዎቹ ሁሉ እዚያ ከተሰበሰቡ በኋላ እረኞቹ ድንጋዩን አንከባለው ከጒድጓዱ ውሃ ያጠጡአቸው ነበር፤ መንጋዎቻቸውን ካጠጡ በኋላ ግን ድንጋዩን መልሰው በጒድጓዱ አፍ ላይ ይከድኑታል። ያዕቆብም እረኞቹን “ወዳጆቼ ሆይ፥ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “እኛ የመጣነው ከካራን ነው” አሉት። እርሱም “የናኮርን የልጅ ልጅ ላባን ታውቁታላችሁን?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “አዎ፥ እናውቀዋለን” አሉት። እርሱም “ለመሆኑ እርሱ ደኅና ነውን?” አላቸው። እነርሱም “አዎ፥ ደኅና ነው፤ እንዲያውም ልጁ ራሔል ያቺውልህ በጎች እየነዳች በመምጣት ላይ ነች” አሉት። ያዕቆብም “ጊዜው ገና ቀን ነው፤ መንጋዎቻችሁንም ወደ ቤት የምታስገቡበት ሰዓት ገና አልደረሰም፤ ታዲያ ለምን ውሃ አጠጥታችሁ አታሰማሩአቸውም?” አለ። እነርሱም “እረኞች ሁሉ መንጋዎቻቸውን ይዘው እዚህ ከመሰብሰባቸው በፊት ምንም ማድረግ አንችልም፤ ሁሉም እዚህ ከመጡ በኋላ ግን ድንጋዩን በኅብረት አንከባለን በጎቹን እናጠጣቸዋለን” አሉት። ያዕቆብም ከእረኞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ ራሔል የአባትዋን በጎች ይዛ ወደዚያ መጣች፤ እርስዋ የበጎች እረኛ ነበረች። ያዕቆብ ያጐቱን የላባን በጎች እየነዳች ስትመጣ ራሔልን አይቶ ወደ ጒድጓዱ ሄደ፤ ጒድጓዱ የተከደነበትንም ድንጋይ አንከባሎ በጎቹን አጠጣቸው። ከዚህ በኋላ ራሔልን ሳማት፤ ከደስታውም ብዛት የተነሣ አለቀሰ፤ “እኔ የአባትሽ እኅት የርብቃ ልጅ ነኝ” አላት። እርስዋም ለአባቷ ልትነግር ሮጣ ሄደች። ላባም የእኅቱ ልጅ ያዕቆብ መምጣቱን በሰማ ጊዜ ሊቀበለው ፈጥኖ ሄደ፤ ዐቅፎ ከሳመውም በኋላ ወደ ቤት አመጣው፤ ያዕቆብ የሆነውን ሁሉ ለላባ ነገረው፤ ላባም “በእርግጥ አንተ ቅርብ የሥጋ ዘመዴ ነህ” አለው፤ ያዕቆብም አንድ ወር ያኽል ከአጐቱ ጋር ተቀመጠ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}