ዘፍጥረት 29:1-14

ዘፍጥረት 29:1-14 NASV

ያዕቆብም ጕዞውን ቀጠለ፤ የምሥራቅም ሰዎች ወደሚኖሩበት ምድር ደረሰ። እዚያም በአንድ ሜዳ ላይ ሦስት የበግ መንጋዎች ተኝተው በነበሩበት አጠገብ የውሃ ጕድጓድ አየ። የበግ መንጋዎቹ የሚጠጡት ከዚሁ ጕድጓድ ሲሆን፣ የጕድጓዱም አፍ ትልቅ የድንጋይ መክደኛ ነበረው። መንጎቹ ሁሉ በጕድጓዱ አጠገብ በሚሰበሰቡበት ጊዜ፣ እረኞች ድንጋዩን ያንከባልሉና በጎቹን ውሃ ያጠጣሉ፤ ከዚያም ድንጋዩን በቦታው መልሰው የጕድጓዱን አፍ ይገጥሙታል። ያዕቆብም እረኞቹን፣ “ወንድሞቼ፤ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ከካራን ነን” አሉት። እርሱም፣ “የናኮርን የልጅ ልጅ ላባን ታውቁታላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን እናውቀዋለን” አሉት። ያዕቆብም፣ “ለመሆኑ ደኅና ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን ደኅና ነው፤ ልጁም ራሔል እነሆ፤ በጎች እየነዳች በመምጣት ላይ ናት” አሉት። ያዕቆብም፣ “እንደምታዩት ጊዜው ገና ነው፤ መንጎቹ የሚገቡበት ሰዓት አይደለም፤ ታዲያ፣ ለምን በጎቹን አጠጥታችሁ ወደ ግጦሽ አትመልሷቸውም?” አላቸው። እነርሱም፣ “መንጎቹ ሁሉ ተሰብስበው ድንጋዩ ከጕድጓዱ አፍ ካልተንከባለለ በቀር አንችልም፤ ከዚያም በጎቹን እናጠጣቸዋለን” አሉ። ያዕቆብ ከእረኞቹ ጋራ በመነጋገር ላይ ሳለ፣ ራሔል፣ እረኛ ነበረችና የአባቷን በጎች እየነዳች መጣች። ያዕቆብ የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልን፣ እንዲሁም የአጎቱን የላባን በጎች ሲያይ፣ ወደ ጕድጓዱ ሄዶ ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ አንከባለለ፤ የአጎቱንም በጎች አጠጣ። ከዚያም ያዕቆብ ራሔልን ሳማት፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ። ያዕቆብም የአባቷ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል ነገራት፤ እርሷም ሮጣ ሄዳ ይህንኑ ለአባቷ ነገረችው። ላባም የእኅቱ ልጅ ያዕቆብ መምጣቱን እንደ ሰማ ሊቀበለው ፈጥኖ ወጣ። ዐቅፎ ከሳመውም በኋላ፣ ወደ ቤቱ ይዞት ሄደ። ያዕቆብም ሁኔታውን ሁሉ ለላባ ነገረው። ላባም ያዕቆብን፣ “አንተማ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ ነህ” አለው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}