ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ምድር ሕይወት ያላቸው ፍጥረቶችን፥ እንደየዐይነታቸው እንስሶችን፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችንና አራዊትን እንደየዐይነታቸው ታስገኝ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር የምድር አራዊትን በየዐይነቱ፥ እንስሶችን በየዐይነታቸው በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችን በየዐይነታቸው ፈጠረ። እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችንና በአምሳያችን እንፍጠር፤ ሰዎችም በባሕር ውስጥ በሚኖሩ ዓሣዎች፥ በሰማይ በሚበርሩ ወፎች፥ በእንስሶችና በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ በሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች፥ እንዲሁም በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎም ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም “ብዙ፤ ተባዙ፤ ዘራችሁ ምድርን ይሙላ፤ ምድርም በቊጥጥራችሁ ሥር ትሁን፤ በባሕር ውስጥ በሚኖሩ ዓሣዎች፥ በሰማይ በሚበርሩ ወፎችና በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራችሁ” ብሎ ባረካቸው። እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ምግብ እንዲሆኑአችሁ በምድር ገጽ ላይ የሚገኙትን የእህል አዝርዕትንና ዘር በውስጡ ያለውን ፍራፍሬ የሚያስገኙ ተክሎችን ሁሉ ሰጥቻችኋለሁ። እንዲሁም በምድር ላይ ለሚኖሩ እንስሶች ሁሉ፥ በሰማይ ለሚበርሩ ወፎች ሁሉ፥ በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ ለሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሁሉ፥ በአጠቃላይ የሕይወት እስትንፋስ ላለው ፍጥረት ሁሉ ምግብ እንዲሆናቸው ልምላሜ ያለውን ሣርና ቅጠል ሁሉ ሰጥቻቸዋለሁ።” እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔር የፈጠረውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፥ እጅግ መልካም ነበረ። ቀኑ መሸ፤ ሌሊቱ ነጋ፤ ስድስተኛ ቀን ሆነ።
ኦሪት ዘፍጥረት 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 1:24-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos