እግዚአብሔር፣ “ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትንና የዱር እንስሳትን እያንዳንዱን እንደ ወገኑ ታስገኝ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔር የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን እንደየወገናቸው፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትን እንደየወገናቸው አደረገ። እግዚአብሔርም ይህ መልካም እንደ ሆነ አየ። እግዚአብሔር፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም፣ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ግዟቸው” ብሎ ባረካቸው። እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “በምድር ላይ ያሉትን ዘር የሚሰጡ ተክሎችን ሁሉ፣ በፍሬአቸው ውስጥ ዘር ያለባቸውን ዛፎች ሁሉ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ ሰጥቻችኋለሁ። እንዲሁም ለምድር አራዊት ሁሉ፣ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፣ በምድር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ማንኛውም ለምለም ተክል ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ” እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ። መሸ፤ ነጋም፤ ስድስተኛ ቀን።
ዘፍጥረት 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 1
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 1:24-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos