ከዚህ በኋላ አገረ ገዢው ታተናይ፥ ሸታርቦዝናይና የእነርሱም ተባባሪዎች የሆኑ ባለሥልጣኖች ንጉሠ ነገሥቱ እንዳዘዛቸው ሁሉንም ነገር ፈጸሙ። የአይሁድ መሪዎች፥ ነቢያቱ ሐጌና ዘካርያስ እያበረታቱአቸው የቤተ መቅደሱን ሥራ አፋጠኑት፤ በእስራኤል አምላክ ፈቃድ የፋርስ ነገሥታት ቂሮስ፥ ዳርዮስና አርጤክስስ ባዘዙትም መሠረት የቤተ መቅደሱን ሥራ ፈጸሙ፤ የቤተ መቅደሱን ሥራ የፈጸሙትም ዳርዮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ የሚጠራው ወር በገባ በሦስተኛው ቀን ነበር። ከዚህም ቀጥሎ የእስራኤል ሕዝብ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ እንዲሁም ከምርኮ የተመለሱት ሌሎችም ሰዎች ሁሉ፥ የቤተ መቅደሱን ምረቃ በዓል በደስታ አከበሩ። እነርሱም ሁሉ ለበዓሉ የሚሆኑትን አንድ መቶ ወይፈኖችን፥ ሁለት መቶ በጎችንና አራት መቶ ጠቦቶችን ለመሥዋዕት አቀረቡ፤ ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚሆኑም ዐሥራ ሁለት ፍየሎችን በእያንዳንዱ ነገድ ስም አቀረቡ። በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈውም መመሪያ መሠረት በኢየሩሳሌም ለተሠራው ቤተ መቅደስ አገልግሎት፥ ካህናቱን በየክፍላቸው፥ ሌዋውያኑን በየቡድናቸው አደራጁ። ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል አከበሩ። ካህናቱና ሌዋውያኑም ሁሉ በሥርዓቱ መሠረት ራሳቸውን አነጹ፤ ሌዋውያኑም በፋሲካው በዓል አከባበር ላይ ከምርኮ ለተመለሱት ሕዝብና ለካህናቱ፥ እንዲሁም ለራሳቸው የቀረቡትን እንስሶች ዐረዱ። መሥዋዕቱንም ሁሉ ከምርኮ የተመለሱት እስራኤላውያን እንዲሁም በዚያች ምድር የሚኖሩትን የአሕዛብን ሥርዓት ትተው የነበረውን ልማድ ትተው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሁሉ እንዲመገቡት ተደረገ። እግዚአብሔር ራሱ በአሦር ንጉሠ ነገሥት ዘንድ መወደድን አግኝተው የእስራኤል አምላክ የሚመሰገንበትን ቤተ መቅደስ እንደገና መሥራት ይችሉ ዘንድ በሥራቸው ሁሉ እንዲረዳቸው ስላደረገላቸው የቂጣን በዓል ሰባት ቀን ሙሉ በታላቅ ደስታ አከበሩ።
መጽሐፈ ዕዝራ 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዕዝራ 6:13-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች