ትንቢተ ሕዝቅኤል 23:40-49

ትንቢተ ሕዝቅኤል 23:40-49 አማ05

“ወንዶችን ከሩቅ አገር ጋብዘው እንዲያመጡላቸው ደጋግመው መልእክተኞችን ላኩ፤ የፈለጓቸውም ወንዶች መጡላቸው፤ ሁለቱ እኅትማማቾች ገላቸውን ታጠቡ፤ ዐይናቸውን ተኳሉ፤ ጌጣጌጦቻቸውንም አደረጉ፤ በተዋቡም ድንክ አልጋዎች ላይ በፊት ለፊታቸው ተቀመጡ፤ እኔ የሰጠኋቸው ዕጣንና የወይራ ዘይት ሳይቀር ብዙ መልካም ነገሮችን በጠረጴዛ ላይ ደረደሩ። የብዙ ሁከተኞች ድምፅ በአካባቢአቸው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር ከበረሓ የመጡ ሰካራሞች ነበሩ፤ ሰካራሞቹም በሴቶቹ ክንዶች ላይ አምባር፥ በራሶቻቸውም ላይ የተዋቡ አክሊሎችን አደረጉላቸው። እኔም በልቤ ‘እነዚህ ወንዶች ዝሙት የሚፈጽሙት በአመንዝራነት ሰውነትዋ ካለቀ ሴት ጋር ነው’ አልኩ። ወንዶች ወደ አመንዝራ ሴቶች እንደሚሄዱ ሁሉ፥ እነዚያም ከበረሓ የመጡ ወንዶች ኦሆላና ኦሆሊባ ከተባሉት ከእነዚያ ከረከሱ ሴቶች ጋር አመነዘሩ። ማመንዘር ስለ ለመዱና እጆቻቸውም በደም ስለ ተበከሉ፥ በእነዚያ በአመንዝሮቹና በነፍሰ ገዳዮቹ ላይ ጻድቃን ይፈርዱባቸዋል።” ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “በእነርሱ ላይ ሁከተኞችን ሰብስብ፤ እነርሱንም ለብዝበዛና ለሽብር አሳልፈህ ስጣቸው። ሁከተኞችንም በድንጋይ ይውገራቸው፤ በሰይፍም ይቈራርጧቸው፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ይግደሉ። ቤቶቻቸውንም በእሳት ያቃጥሉ። እናንተ ሁለት እኅትማማቾች እንዳመነዘራችሁ ሁሉ ሴቶች ከእንግዲህ ወዲህ እንዳያመነዝሩ መቀጣጫ ይሆን ዘንድ ከምድሪቱ ሁሉ ላይ የሴሰኝነት ስድነት እንዲወገድ አደርጋለሁ። እናንተም ሁለት እኅትማማቾች ስለ ስድነታችሁና ለጣዖቶች በመስገድ ስለ ፈጸማችሁት ኃጢአት እቀጣችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ ልዑል እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”