ሕዝቅኤል 23:40-49

ሕዝቅኤል 23:40-49 NASV

“ከዚህም በላይ ወንዶች ከሩቅ እንዲመጡላቸው መልእክተኛ ላኩ፤ እነርሱም መጡ። አንቺም ገላሽን ታጥበሽ፣ ዐይንሽን ተኵለሽና በጌጣጌጥ ተውበሽ ጠበቅሻቸው። በተዋበ ዐልጋ ላይ ተቀመጥሽ፤ ዕጣኔንና ዘይቴን ያኖርሽበትንም ጠረጴዛ ከዐልጋው ፊት ለፊት አደረግሽ። “የሚፈነጥዙ ሰዎች ድምፅ በዙሪያዋ ነበር፤ ከሚያውኩ ሰዎች ጋራ ከበረሓ የመጡ ሰካራሞች ነበሩ፤ በሴትየዋና በእኅቷም ላይ አንባር፣ በራሳቸውም ላይ የተዋበ አክሊል አደረጉላቸው። እኔም በአመንዝራነት ሰውነቷ ስላለቀው፣ ‘እርሷ ሕይወቷ ይኸው ስለ ሆነ እንደ ዝሙት ዐዳሪ ይጠቀሙባት’ አልሁ። እነርሱም ከርሷ ጋራ ተኙ፤ ሰው ከአመንዝራ ሴት ጋራ እንደሚተኛ ከእነዚያ ባለጌ ሴቶች፣ ከኦሖላና ከኦሖሊባ ጋራ ተኙ። ጻድቃን ግን ለአመንዝራና ለነፍሰ ገዳይ ሴቶች የሚገባቸውን ፍርድ ይፈርዱባቸዋል። አመንዝሮች ናቸውና፤ እጃቸውም በደም ተበክሏል። “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሕዝብን ቀስቅሰህ አምጣባቸው፤ ለሽብርና ለዝርፊያም አሳልፈህ ስጣቸው። ሕዝቡ በድንጋይ ይወግራቸዋል፤ በገዛ ሰይፋቸው ይቈራርጣቸዋል፤ ወንድና ሴት ልጆቻቸውን ይገድላል፤ ቤቶቻቸውንም ያቃጥላል። “ስለዚህ ሴቶች ሁሉ እንዲጠነቀቁና መጥፎ ፈለጋችሁን እንዳይከተሉ፣ ሴሰኛነትን ከምድሪቱ አጠፋለሁ። የሴሰኝነታችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ፤ ጣዖት በማምለክ ለፈጸማችሁት ኀጢአት ቅጣት ትሸከማላችሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።”